🔇Unmute
አዳማ፣ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፡- በአዳማ ከተማ አስተዳደር በከተማ ግብርና የተሰማሩ ነዋሪዎች ከዘርፉ በሚያገኙት የተሻለ ገቢ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገለጹ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እና የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተተገበረ ያለው "የሌማት ትሩፋት" እና የከተማ ግብርና ንቅናቄ፣ የከተማ ነዋሪዎች ያሏቸውን አነስተኛ ቦታዎች ወደ ልማት እንዲቀይሩ እያስቻለ ይገኛል።

በአዳማ ከተማ አስተዳደርም በዘርፉ ለተሰማሩ ነዋሪዎች በጓሮ አትክልት፣ በወተት ላም፣ በዶሮ እና በንብ ማነብ ስራዎች ተሰማርተው የራሳቸውን ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው።

ከተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር መንግሥቱ ረጋሳ በሰጡት አስተያየት በሰብልና አትክልት ልማት በመሳተፍ እያገኙ ያሉት ምርት ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ አስገኝቶላቸዋል።
በተለይም የበቆሎ ሰብልን በሄክታር እሰከ 120 ኩንታል፣ ጤፍ ደግሞ በአማካይ 16 ኩንታል በማምረትውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የግብርና ባለሙያዎች በሚያደርጉላቸው የቴክኒክ ድጋፍ በመታገዝም የአዋሽ ወንዝን በመስኖ በመጥለፍ ስንዴ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም በማልማት የገቢ ምንጫቸውን ማስፋት እንደቻሉ ተናግረዋል።

ሌላኛው የልማቱ ተሳታፊ በከተማው የአዋሽ መልካሳ ወረዳ አርሶ አደር ሹራ በቀለ በበኩላቸው መንግስት ያመቻቸላቸውን እድል በመጠቀም ከሰብል ልማት በተጓዳኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ ፓፓያ ማልማት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ልማቱን ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በኩታገጠም እያለሙ መሆናቸውን ጠቅሰው በተለይ የመስኖ ውሃንና የምርት ማሳደጊያ ግበዓት በአግባቡ በመጠቀም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየተጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ላለሙት ፓፓያ መንግስት የገበያ ትስስር በማመቻቸቱ የተሻለ ገቢ በማግኘት ቤተሰባቸውን ከማስተዳደር ባለፈ ጥሪት በማፍራት ውጤታማ እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ አጋርተውናል።
በቀጣይም የፍራፍሬ ልማቱን በማስፋት የግብርና ምርትና ምርታማነት በመጠንና በጥራት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ማቀዳቸውን አርሶ አደሩ አስታውቀዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ በከተማ ግብርና ልማት ዘርፍ ያሉ ጸጋዎችን በመለየት ውጤታማ ስራ ማከናወን ተችሏል።
በተለይም አርሶ አደሮችንና በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶችን በኩታገጠም በሰብል፣ በወተትና በዶሮ እርባታ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ማሰማራት መቻሉን ገልጸዋል።
እስካሁን 30 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች 13 በሚሆኑ አዳዲስ የከተማ ግብርና ኢንሼቲቮች በማሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ከተማዋ ያላትን የውሃና ለም መሬት በማቀናጀት ተግባራዊ የተደረገው የከተማ ግብርና የስራ አጥነት ችግርን በማቃለል አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን አመልክተዋል።
በተለይም የአዋሽ ወንዝን በመጥለፍ ለልማት በማዋል ከአትክልትና ፍራፍሬ ባሻገር የመስኖ ስንዴን በስፋት በማልማት ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።

በእንቅስቃሴያቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ የንብ ቀፎ፣ የመስኖ ውሃ መሳቢያ ሞተርን ጨምሮ ሁሉንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ መስራቱን አብራርተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በኩታገጠም የተጀመረው የፍራፍሬ ልማት ውጤታማ በመሆኑ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን፣ ሙዝና ሌሎችም ፍራፍሬዎች በስፋት እየለሙ እንደሚገኙ ከኃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
ጎንደር ፤ህዳር 2/2019 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዘላቂ የምጣኔ ሃብት እድገትና ለብሔራዊ ደህንነቷ መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን የዩኒቨ...
Nov 12, 2026
አዲስ አበባ በለውጥ ጉዞዋ ውስጥ የጀመረችውን የከተማ ልማት እንቅስቃሴ ግለት ሳታስቀይር፣ የዘላቂ መሠረተ ልማት ግንባታዋን በማፋጠን ወደ ተቀናጀና ዘመናዊ ከተማ...
Nov 9, 2026
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ታንዛኒያ በካፒታል ገበያ ዘርፍ ተቋማዊ የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ትብብራቸውን ለማጎልበት ቁርጠኞች መሆና...
Oct 29, 2026
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት ዋና ዓላማ ያሉትን ሀብቶች አውቆና አበልጽጎ ለተከታዩ ትውልድ የሚተርፍ ወረት መፍጠር መሆኑን የኢፌ...
Oct 16, 2026