🔇Unmute
ሮቤ ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):-በኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቱሪዝም ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭና አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን የዘርፉ ምሁራን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ቱሪዝም አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር!” በሚል በሰጡት ማብራሪያ በዘርፉ ልማት የተከናወኑ ተግባራትንና የመጡ ውጤቶችን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የብዝሃ የኢኮኖሚ አማራጮችን መሰረት አድርጎ በመስራት በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት በማሳያ አስቀምጠዋል።
በተለይም በባሌ አካባቢ የሚገኙ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ ድሬ ሼህ ሁሴን፣ ባሌ ተራሮችን ጨምሮ ሌሎች የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ግንባታ፣ የከተሞች ኮሪደር ልማትና የቅርሶች እድሳት ለቱሪዝም ዘርፉ እድገትና ማንሰራራት ትልቅ አቅም መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ዘርፍ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሌ ዞንን እምቅ የቱሪዝም አቅም በልዩ ሁኔታ የገለጹበት መንገድ ለዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው መምህርና የዘርፉ ተመራማሪ ስንታየሁ አይናለም(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የባሌ ዞን የተለያዩ ሥነ-ምህዳሮች በአንድ ላይ የሚገኙበት መሆኑ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የቱሪዝም መስህቦችን በማልማት፣ የጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘምና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ረገድ የተሻሉ ተግባራት የተከናወኑበት መሆኑን ምሁሩ ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱሪዝም ልማት ኢኒሼቲቮች አጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቁት መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪው፤ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በምርምር ለመለየት የአምስት ዓመት ሜጋ ፕሮጀክት ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝም አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዞኑን እምቅ አቅም በይፋ መጥቀሳቸው፣ ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸው፤ የግንባታ ሥራቸው የተጀመሩ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች ሲሟሉ ዘርፉ የኢኮኖሚው ምሰሶ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የባሌ ዞን ብዙም ባልተራራቁ አካባቢዎች የተለያዩ ዓይነት ሥነ-ምህዳሮች በቀላሉ የሚታዩበትና ለቱሪስት ተመራጭና ተወዳጅ የሆኑ ቅርሶች መገኛ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ ሀዲስ ታደለ(ዶ/ር) ናቸው።
የለውጡ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የእነዚህን መስህቦች ልማት ወደ ተግባር በማስገባት ላይ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ከዚህ በፊት በዋናነት ከሚታወቁት ዋና ዋና ቅርሶች ባሻገር ከ100 በላይ አዳዲስ ቅርሶች በጥናት መለየታቸውንና የተለዩት ቅርሶችም በሳይንሱ ዓለም እንዲታወቁ ዲጂታል ካርታ የተዘጋጀላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እያካሄዱ በሚገኙት ጥናት በባሌ፣ ምሥራቅ ባሌና ምዕራብ አርሲ አካባቢ የሚገኙ የተለያዩ የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ የመስህብ ስፍራዎች ተለይተው፣ ዶክመንት ተሰንዶላቸው መቀመጣቸውን ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱሪዝም ኢኒሼቲቭ ለዘርፉ ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት ምሁራኑ፣ የባሌ ዞንን የተፈጥሮና ባህላዊ ሃብቶችን በማዘመንና በምርምር በማገዝ የሀገሪቱን የቱሪዝም ገጽታ ለመቀየር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
አዳማ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ቡናን ከመደበኛ ወቅት በተጨማሪ በበጋ መስኖ በማልማት የአምራቹን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መደ...
Jun 17, 2026
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣዮቹ 90 ቀናት የከተማዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ላ...
Jun 17, 2026
ሀዋሳ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ ሀዋሳ ከተማን በማልማት የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከልነቷን ይበልጥ ለማሳደግ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚ...
Jun 14, 2026
ጋምቤላ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ውስጥ ከ72 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ...
Jun 11, 2026