🔇Unmute
ነቀምቴ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ወለጋ ዞን በ2018/19 የመኸር እርሻ ከ184 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ሰብል በኩታ ገጠም መልማቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ምስራቅ ወለጋ ዞን ሰፊ እና ለም አመቺ የእርሻ መሬት እንዲሁም በቂ የዝናብ መጠን ካላቸውና ዋነኛ የግብርና ምርት ቀጠናዎች አንዱ ሲሆን፤ በአካባቢው በስፋት ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል የበቆሎ ምርት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በዞኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ አርሶ አደሮችን በማደራጀት በኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ እንዲያለሙ፣ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን፣ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያን በስፋት እንዲጠቀሙ ለማስቻል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ግብርና ፅህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ደረጄ ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በምርት ዘመኑ በዞኑ 831 ሺህ 816 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል።

በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 184 ሺህ 879 ሄክታሩ በኩታ ገጠም በበቆሎ ሰብል መሸፈኑን ጠቁመው፤ ከዚህም ወደ 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች በስፋት ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል የበቆሎ ምርት ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው፣ እንደ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ስንዴና ገብስ ያሉ የጥራጥሬ ሰብሎችና የቅባት እህሎችም በስፋት እንደሚመረቱ ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ይበልጥ ውጤታማና ምርታማ እንዲሆን ለማስቻል፤ በየደረጃው በሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት የሚደረገው የሙያ ድጋፍ፣ የቴክኖሎጂና የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም የቅርብ ክትትል ተጠናክሮ መቀጠሉን አክለው ገልጸዋል።
በዞኑ የበቆሎ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከቀረበው 550 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ 400 ሺህ ኩንታሉ ለአርሶ አደሮቹ መሰራጨቱን ተናግረዋል።
ከምርጥ ዘር አንጻርም 32 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር መቅረቡን ገልጸው፣ በልማቱም ከ152 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

በዞኑ በልማቱ እየተሳተፉ ከሚገኙት አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አብዱ ስጦታው እንደተናገሩት፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኩታ ገጠም የአሰራር ዘዴ በቆሎን በስፋት ሲያለሙ ቆይተዋል።
በዚህም ባለፈው ዓመት ምርታማነታቸው መሻሻሉንና ምርጥ ዘርን በመጠቀም ከአንድ ሄክታር መሬት እስከ 43 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አንስተው፣ በዘንድሮው የምርት ዘመንም የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደር አዲሱ ተሾመ በበኩላቸው፤ የግብርና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የቀረበላቸውን ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያን በአግባቡ በመጠቀም ምርታማ ለመሆን በትጋት በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ድሬደዋ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ እያደረገ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ...
Aug 13, 2026
ሮቤ፣ሐምሌ 22/2018(ኢዜአ)፦በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለ...
Jul 30, 2026
ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 22/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት በሰላም፣ በልማትና መልካም አስተዳደር የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ...
Jul 30, 2026
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት አምስት ዓመታት ስር የሰደዱ ችግሮችን በመቅረፍ አዲስ አበባን የሰላምና የልማት ማዕከል ማድረግ መቻሉን የአዲስ...
Jul 18, 2026