🔇Unmute
ጅማ ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦የሚያከናውናቸው ግብርና ተኮር የምርምር ሥራዎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን የጅማ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን ዘርፈ ብዙ የምርምር ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን፣ ግብርና ተኮር የምርምር ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው በጅማ ዞን እና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግም የተፈጥሮ ማዳበሪያን አምርቶ ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያው በባዮቻር (Biochar) ላይ ተመስርቶ የተመረተ ሲሆን፣ የአፈር ጤንነትን በማሻሻል ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ አካባቢን ከኬሚካል ተፅዕኖ ለመጠበቅ እንደሚያግዝም ተመልክቷል።

'ባዮቻር' የእርሻ ተረፈ ምርቶችና የቅጠላ ቅጠል ውጤቶችን በከፍተኛ ሙቀት በማቃጠል የሚገኝ የከሰል ዓይነት ሲሆን ይህም የከሰል ዓይነት የሚዘጋጅበት ዋነኛ ዓላማ ለማገዶነት ሳይሆን የአፈርን ለምነት ጠብቆ ለማቆየት ነው።
በተጨማሪም የአፈር ለምነትን በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ ።
በዩኒቨርሲቲው የግብርና እና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ ምክትል ዲን ፍቅረማርያም ገዳ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከሚያደርጉ የምርምር ስራዎች አንዱ በባዮቻር ላይ የተመሠረተ ማዳበሪያን ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ገልጸው በእስካሁኑ ሂደትም ከ500 በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በአርሲ እና በባቱ ከሚገኙ የምርምር ማዕከላት ጋር በመሆን ለአርሶ አደሩ የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ሲሆን ፤ በተጨማሪም በሲዳማ ክልልም ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በጅማ ብቻ ከ300 በላይ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ከመጠቀም ባሻገር ሥልጠና ወስደው እራሳቸው በማምረት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ቡኖ በደሌ ዞንን ጨምሮ በአጎራባች ዞኖች ለባለሙያዎች እና ለአርሶ አደሮችም ሰፊ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ሚልኪያስ አህመድ (ዶ/ር) ለማዳበሪያው ዝግጅት አስፈላጊ የሆነው ባዮቻር አገልግሎት ላይ ካልዋሉ ተረፈ ምርቶች የሚዘጋጅ መሆኑን አመልክተዋል።

የምርምር ሥራው ላለፉት 12 ዓመታት ሲሞከር እንደነበር የገለጹት ተመራማሪው ከ3 ዓመታት ወዲህ ግን ተጨባጭ ለውጥ በማምጣቱ እንዲስፋፋ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በጅማ ዞን የዴዶ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ቢያ ሀጂ፤ በምርምር ውጤቱ የተገኘውን ማዳበሪያ ተጠቅመው ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተሰጣቸው ሥልጠና መሠረትም ወደ ማምረት ሥራ ገብተው 10 ኩንታል የባዮቻር የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረታቸውን ገልጸዋል።
ሌላው የወረዳው አርሶ አደር ራያ አባፊጣ ፤ተመራማሪዎቹ ባቀረቡት የተፈጥሮ ማዳበሪያን ተጠራጥረው እንደነበር ገልጸው፤ ሆኖም ውጤታማ መሆኑን ካወቅኩ በኋላ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ወደ ማምረት ስራ ገብቻለሁ ብለዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁሉም የጅማ ዞን ወረዳዎች ለማዳረስ እንዲሁም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።
አምቦ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ለንብ ማነብ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ...
Jun 14, 2026
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የበጋ መስኖ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የአርስ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን የክልሉ ምክት...
Jun 11, 2026
ሐረማያ፤ ግንቦት 20/2018 (ኢዜአ)፦ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን እያጎለበተ እንደሚገኝ አስታወቀ። ዩኒቨ...
Jun 1, 2026
ሆሳዕና፣ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የሕብረት ሥራ ማህበራትን ደግፎ የማብቃት ሥራው ተጠናክሮ እ...
May 26, 2026