🔇Unmute
የአንድ ሀገር ታላቅነትና ብልፅግና የሚለካው በገጠሟት ፈተናዎች ስፋት ሳይሆን፣ እነዚያን ፈተናዎች ወደ ልማትና ዘላቂ ስኬት ለመቀየር በሚወሰዱ ቆራጥ ሀገራዊ እርምጃዎች ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ አያሌ መዋቅራዊ፣ጂኦፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን አልፋ የተጓዘች ሀገር እንደመሆኗ መጠን፤በአሁኑ ወቅት የነበሩባትን ማነቆዎች ወደ አዲስ ዕድል በመቀየር ላይ ትገኛለች።
ይህ ሂደት በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በመሬት ላይ በሚታዩ ዘለቄታዊ ታላላቅ ፕሮጀክቶችና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች እውን እየሆነ ይገኛል።
ይህ አዲስ የተግባር ምዕራፍ ደግሞ የሀገሪቱን ዕድገትና ትውልድ ተሻጋሪ ጉዞ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የተነደፈው የመደመር እሳቤ ቀጥተኛ ነጸብራቅ ነው።
የመደመር ፍልስፍና የነበሩ በጎ እሴቶችንና ስኬቶችን ይዞ መቀጠልን፣ጉድለቶችን ማስተካከልን እና አዳዲስ ፈጠራዎችን ማመንጨትን እንደ ስትራቴጂ የሚይዝ በመሆኑ፣በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተተገበሩ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችም ይህንን እሳቤ በተግባር ያረጋገጡ ናቸው።
ለዘመናት ያጋጠሙትን የምግብ ዋስትና ችግሮች፣ የምንዛሬ እጥረትና የገበያ መዛባቶች ለመቅረፍ የተወሰዱት አገራዊ እርምጃዎች የዚሁ ችግርን ወደ እድል የመቀየር ስትራቴጂ ዋና ማሳያ ናቸው።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የስንዴ እህልን ከውጭ ለማስገባት ታወጣ የነበረውን በዓመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረትና አገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትልቅ ታሪካዊ እመርታ አስመዝግቧል።
ሀገሪቱ አሁን ላይ የስንዴ ምርትን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ማብቃት ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ ገበያ ኤክስፖርት ማድረግ ወደምትችልበት ደረጃ ተሸጋግራለች።
በቅርብ የምርት ዘመናት ኢትዮጵያ 33 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ በማምረት በአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች ሀገር ለመሆን የበቃች ሲሆን፣ ይህ ስኬት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ከአቮካዶና ሆርቲካልቸር እስከ አግሮ-ፕሮሰሲንግ ያሉ አዳዲስ አቅሞችን በመጠቀምና አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር የሀገር ውስጥ አምራቾች ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር እንዲገናኙና አገራዊ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲያድግ አስችሏል።
ይህም የመደመር እሳቤ የሀገር ውስጥ አቅምን በመጠቀም የውጭ ጥገኝነትን እንዴት እንደሚቀንስ በተግባር ያሳየበት ተጨባጭ ማሳያ ነው።
በሌላ በኩል የተፈጥሮ ሀብትንና የከተሞችን አቅም ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ ሲፈጠሩ የነበሩትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅፋቶች ለመፍታት አዳዲስ ሀገራዊ የልማት ሞዴሎች በመተግበር ላይ ይገኛሉ።
በዚህም ከተሞችን የዘመናዊና ጤናማ አኗኗር ማሳያ ማድረግ ተችሏል።በዋና ዋና ከተሞች የሚከናወኑት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ ነባር መጨናነቆችን፣ የመሰረተ ልማት እጥረቶችንና የከተማ አስተዳደር ጉድለቶችን በመቅረፍ ከተሞችን ዘመናዊ፣ ፅዱ፣ እና ለኑሮ ተስማሚ አድርገዋቸዋል።
ይህም የከተሞችን ውበትና ደረጃ ከማሳደግ ባሻገር ለንግድ፣ ለቱሪዝም እና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ በገበታ ፕሮጀክቶች አማካይነት ያልተነኩ የተፈጥሮ ውበቶችንና ታሪካዊ ስፍራዎችን ወደ ኢኮኖሚያዊ ሀብትነት በመቀየር እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ ሀላላ ኬላ እና ደምቢ ኢኮ-ሎጂ ያሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቱን የቱሪዝም ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
ይህ የልማት ግንባታ ከመንግስት በጀት ብቻ ሳይሆን በህዝባዊ ተሳትፎና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የታገዘ በመሆኑ የመደመርን የሀብት አጠቃቀም ጥበብ በግልጽ ያሳያል።በተለይም በክረምት ወራት የተከናወኑ በሺዎች የሚቆጠሩ አቅመ-ደካሞችን ቤቶች ማደስ፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል እና አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት የመንግስትን ከፍተኛ በጀት በማስቀረት የላቀ የካፒታል አቅም መፍጠር ችሏል።
የአንድ ሀገር የእድገት ጉዞ የሚረጋገጠው የማህበረሰቡን አስተሳሰብ፣ የፖለቲካ ባህል እና የማህበራዊ ትስስር እሴቶችን በአዲስ መልክ በመገንባት እንደሆነ የመደመር እሳቤ በጥብቅ ያሰምርበታል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ እውነታ ውስጥ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እና ሀገራዊ ምክክር ሀገሪቱን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም እየተተገበሩ ያሉ ተጨማሪ የመዋቅርና የአስተሳሰብ አምዶች ናቸው።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበራዊ ካፒታል ግንባታ እና የወጣትነት ሀይልን ለሀገር ግንባታ የማዋል ፍልስፍና በተግባር የገለጠ ስራ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩነቶችን በኃይል፣በግጭት እና በጠመንጃ የመፍታት አደገኛ ልማድን በማስወገድ፤ በሰለጠነ፣ አሳታፊ እና በውይይት የማመን ባህል የመተካት ትልቅ መሰረት ተጥሏል። ይህም ቀጣይነት ላለው ሀገረ-መንግሥት ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም የሚጠቅም የፖለቲካ ባህል ሽግግር የፈጠረ ሲሆን፣ ልዩነቶችን በመደመር ውበት የመቀየር ጥበብ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የገጠሟትን ዘመናዊና ታሪካዊ ፈተናዎች ወደ ልማትና ወደ ዘላቂ ስኬት የመቀየር ትልቅ አቅም እንዳላት በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
በመደመር ፍልስፍና የሚመሩት እነዚህ ፕሮጀክቶች እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የምታደርገውን የማንሰራራት ጉዞ እውን የሚያደርጉ ናቸው።
የኢትዮጵያ ነገ ብሩህ የሚሆነው ፈተናዎች በሌሉበት ሳይሆን፣ ያሉትን ፈተናዎች በመደመር እሳቤ ወደ ተሻገረ ዕድል የመቀየር አቅሟ እንደሆነ ይህ ታሪካዊ ጉዞ ይመሰክራል።
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫዎች የሀገርን እድገት በማነጽ ረገድ መሰረታዊ ስኬቶችን እያስመዘገቡ መሆኑን ምክትል ጠቅ...
Sep 30, 2026
ቢሻን ጉራቻ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦በቢሻን ጉራቻ ከተማ ለመስቀል በዓል በቂ የእርድ እንስሳት አቅርቦት በመኖሩ በተረጋጋ ሁኔታ እየተገበያዩ መሆናቸው...
Sep 28, 2026
ሐረር፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ):-በሐረሪ ክልል በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆ...
Sep 23, 2026
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት...
Sep 4, 2026