የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የግሉ ዘርፍ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በስራ እድል ፈጠራ ያለውን ሚና ሊያጠናክር ይገባል

Jun 11, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም የግሉ ዘርፍ በስራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሁለተኛው ምዕራፍ 5ኛ ዙር "ስለ ኢትዮጵያ" የፓናል ውይይት "ስራ ዕድል ፈጠራ ስለ ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ ተካሒዷል፡፡


የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልእክት፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሃብቶች የበለፀገች መሆኗን ተከትሎ ሃብቶቿን ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች ነው ብለዋል።

በዚህም ያላትን ጸጋ በመጠቀም የክህሎት ልማትን፣ የስራ ዕድል ፈጠራንና የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትን በማስተሳሰር አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ትግበራው አሳታፊና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

ይህም ዜጎች በሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማጎልበት ምቹ እድል እንደሚፈጥርም አክለዋል።

በዚህ ረገድ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በክህሎት ልማት ላይ ለሚያከናውነው ተግባር ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራው እያገዘ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ የሀገራትን ልምድና ተሞክሮ የቀመረና አዳዲስ የስራ አማራጮችን ተደራሽ ያደረገ የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

ይህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጎልቶ የሚታይ የስራ እድል ተጠቃሚነትን ተደራሽ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩን ነው የጠቀሱት።

የግሉ ዘርፍ በስራ እድል ፈጠራ ላይ ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና ለአካታች ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማጉላት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አካታች፣ አሳታፊና የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

መንግስት የስራ እድል ፈጠራ አማራጮችን ለማስፋት እያከናወነ ያለው ተግባር የግሉን ዘርፍ ይበልጥ የሚያበረታታና በዘርፉ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲጨምር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።


የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ እንደገለጹት ስታርታፖችን በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂና በእውቀት ሽግግር ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ የስታርትአፕ አዋጅ መዘጋጀቱን ትልቅ ውሳኔ ነው ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ በዘርፉ የሚስተዋለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ከማቃለል በዘለለ የቴክኖሎጂ አሰራርን በመጠቀም የተሻሻሉና አዳዲስ ምርቶችን ለማስፋት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ፥ የግሉ ዘርፍ ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።


የሚፈጠሩ የስራ እድሎች አምራችነትን የሚያበረታቱ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸው፤ የግሉ ዘርፍ በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ከመንግስት ጋር ያለውን ትብብር ሊያጠናክር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የቲኖ ማርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወጣት ኢዘዲን ካሚል የቴክኖሎጂ ክህሎትን በማስረጽና በመተግበር ወቅቱ የሚጠይቀውን ተወዳዳሪነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብሏል።


ወጣቶች በመንግስት የተመቻቹ እድሎችን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አንስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአዳማ ከተማ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ማህበራትና አምራቾች የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.