የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የሀገርን እድገት መሰረት ያደረገ ነው

Jan 16, 2026

IDOPRESS

🔇Unmute

መቀሌ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የሀገርን እድገት መሰረት ያደረገ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በስኬት ተጠናቆ በሚቀጥሉት አምስት አመታት የሚተገበር ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ መደረጉ ይታወቃል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዲጂታል አገልግሎት መሰረታዊ የሚባል ለውጥና ተጨባጭ የሚባሉ ውጤቶች የተመዘገቡበት ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።

በዚህ ረገድ በተለይም በፋይናንስ አገልግሎቶች መሰረታዊ የሚባል የአሰራር ለውጥ በማምጣት አገልግሎታቸውን ይበልጥ በማሻሻል ላይ ሲሆኑ የቴሌ ብር እና ሌሎችም የዲጂታል አገልግሎቶች ሌላ እድል ይዘው መጥተዋል።

በእነዚህና ሌሎች ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እቅድ ትግበራ የላቀ ስኬት የተመዘገበበት በመሆኑ ከዚህ ተሞክሮ በመሰነቅ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የላቀ ስኬት ለማምጣት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

በአጠቃላይ በዲጂታል ልማት ትግበራና ቀጣይ እቅዶች ላይ ኢዜአ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ የዜጎችን ተጠቃሚነትና የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ የእርሻና ባዮ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ተማራማሪ እያሱ አብርሃ(ዶ/ር)፤ በዲጂታል እቅድና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ አስደናቂ ጉዞ ላይ መሆኗ በተግባር እየታየ ነው ብለዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ከሚባለው በላይ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አንስተው የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድም በውጤታማነት የሚተገበር እንደሚሆን አመላክተዋል።

የዲጂታል 2030 ስትራቴጂክ እቅድ ከገጠር እስከ ከተማ ሁሉን አቀፍ የህዝብ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው በተለይም ለአርሶ አደሩ አጠቃላይ መረጃ፣ የምርት ገበያ ሁኔታ፣ የብድር አቅርቦትና አገልግሎቶችን በዲጅታል መጠቀም የሚያስችል ይሆናል ብለዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ፍትሃዊ የግብርና ግብአትና ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የዲጂታል ትግበራው ከፍተኛ እገዛ የሚኖረው መሆኑንም አስረድተዋል።

በድምሩ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የሀገርን እድገት መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ አስተባበሪ አብርሃ ኪዳነማርያም (ዶ/ር)፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ ትግበራ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቴሌኮም ተደራሽነትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በገጠርም ይሁን በከተማ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል።

የእቅዱ ትግበራ በተለይም በገጠር የአርሶ አደሩን ህይወት ቀለል የሚያደርግና እንግልትን የሚያስቀር በመሆኑ ልዩ ትርጉም ያለው በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉም አካላት ትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማሳካትና የአርሶ አደሩን የገንዘብ እንቅስቃሴ በማዘመን በቀላሉ የብድር አገልግሎትና የገበያ አማራጮችን እንዲያይም ትልቅ እድል መሆኑን አስረድተዋል።

ለእቅዱ መሳካት የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ የግሉም ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ባለሙያዎቹ በትብብር የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ማሳካት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.