🔇Unmute
አዲስ አበባ፤መጋቢት 22/2018(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነዳጅን በቁጠባ በመጠቀም የነዳጅ አቅርቦት ችግርን በጋራ ማለፍ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በመካካለኛው ምስራቅ ያለው ጦርነትና አለመረጋጋት በሀገራችን የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ እንዲሁም መንግሥት የሚከተላቸውን አቅጣጫዎች በተመለከተ ትናንት ለኢዜአ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።
በማብራሪያቸውም ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በሀገርና በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳያሳድርና በፍትሐዊነት ለመምራት መንግሥት ተግባራዊ የሚሆን የቅድሚያ አሰጣጥ ውሳኔ ማሳለፉን ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል።
በዚህም የነዳጅ አቅርቦት የሚያገኙ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው፤ ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣ ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች በቀጥታ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ እንዲያገኙ መወሰኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች፣ ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮች፣ የከተማና ሀገር አቀፍ የብዙሃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም በናፍጣ የሚሰሩ ሌሎች ለህብረተሰብ ግልጋሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ የቅድሚያ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራር የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።
የደብረታቦር ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሰለሞን አበጋዝ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በሀገራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።
ለአብነትም የመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጦርነትና አለመረጋጋትን በማንሳት ይህም ነዳጅን በሚፈለገው ደረጃ ለማግኘት አዳጋች እያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ችግሩን ለመቋቋም ተቋማቶች የነዳጅ አጠቃቀማችንን በቁጠባ እንዲሆን ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
ለዚህም በዩኒቨርሲቲያቸው ነዳጅን በቁጠባ አገልግሎት ላይ ለማዋል የሚያስችሉ አካሄዶችን እያጤነ መሆኑን ተናግረዋል።
የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው አሁናዊ ሁኔታ የነዳጅ አቅርቦት ችግር እየፈጠረ ይገኛል።
ይህም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሳለጥ አኳያ እንቅፋት መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን ለማለፍም እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ተቋማቶች የስራ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነዳጅን መቆጠብ የሚያስችሉ አካሄዶችን መከተል እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ ዩንቨርሲቲው ከዚህ አኳያ ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመተግበር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ይህን ችግር በጋራ ለማለፍ ህብረተሰቡ ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀም፣ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን የመጠቀም ስልትን መከተል፣ የእግር ጉዞ ባህልን ማጎልበት፣ አላስፈላጊ የጉዞ ፕሮግራሞችን መሰረዝና ማቆም፣ የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም፣ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ ቀርቧል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025