🔇Unmute
ጊምቢ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ወለጋ ዞን በመኸር ወቅት ከለማው የሩዝ ሰብል ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፈይሳ ሀምቢሰ እንደገለጹት በክረምት የመኸር እርሻ 460 ሺህ ሄክታር መሬት የለማ ሲሆን ከዚህ ወስጥ ከ162 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በሩዝ ሰብል የለማ ነው፡፡
በሩዝ ከለማው መሬትም ከ5 ሚሊዮን 749 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

መንግስት የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ከነደፋቸው የግብርና ኢኒሸቲቮች የሩዝ ሰብል ልማት አንዱ እንደሆነ አስታውሰው፣ ልማቱ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት እያሳደገው ነው ብለዋል፡፡
የሩዝ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም የግብአት አቅርቦትና የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ ፈይሳ አክለዋል።
አርሶ አደሮቹ ቤተሰቦቻቸውን በማስተባበርና ሌሎች አደረጃጀቶችን በመጠቀም ለሩዝ ሰብል እንክብካቤ በማድረጋቸው በአሁኑ ወቅት የሰብሉ ቁመና በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አርሶ አደሩ ከሩዝ ሰብል የእንክብካቤ ስራ ጎን ለጎን ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዝግጅት እንዲያደርግና በመኽር እርሻው ከለማው ቀድሞ የደረሰን ሰብል ብክነትን በቀነሰ መልኩ እንዲሰበሰብ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡
በሩዝ ልማቱ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ጌታሁን ጉታታ እንደተናገሩት፤ በግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ በሩዝ ልማት ሥራ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ሰብሉን በኩታ ገጠም ከማልማት ባለፈ በጋራ የአረምና የተባይ ቁጥጥር በማድረጋቸው ከሩዝ ሰብሉ ልማት ከ40 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በቡና ልማት ላይ ብቻ ተወስነው እንደነበረና ኑሮዋቸውም ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ባገኙት ግንዛቤ በሩዝ ልማትና በበጋ መስኖ የተለያዩ ሰብሎች በማልማት ገቢያቸው ማደጉን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው አርሶ አደር ዮሴፍ ሙሉነህ በበኩላቸው ቀደም ሲል ከሚያመርቱት የበቆሎ ሰብል በተጨማሪ በሩዝ ሰብል ልማት በመሰማራት ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በሩዝ ልማት ምርታማ መሆናቸውን ገልጸው በባለሙያ የሚሰጠውን ምክረ ሀሳብ በመጠቀም ለሰብሉ ተገቢ እንክብካቤ ማድረጋቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡
በኢንሼቲቭ ተቀርጸው እየተተገበሩ ያሉ የግብርና ልማቶች እሳቸውን ጨምሮ የሌሎች የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመኸር የሩዝ ሰብል ስራቸው ጎን ለጎን በበጋ መስኖ ስንዴን ለማልማት እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ሀዋሳ፣ ነሐሴ20/2018 (ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ የሐይቅ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ...
Aug 27, 2026
ሐረሪ ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና መሬት ወስደው ወደ ግንባታና ማምረት ባልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ የኢንቨስትመንት...
Aug 14, 2026
ደሴ፤ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ173 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠ...
Aug 13, 2026
ባሕር ዳር ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር...
Jul 31, 2026