ቡሌ ሆራ፤ ጥር 3/2017(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጉጂ ዞን የተሻሻለውን የግብርና አሰራር የተገበሩ አርሶ አደሮች ምርታቸው ከቀደመው ጊዜ በተሻለ መልኩ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡
ከዞኑ የመኸር አዝመራ እስካሁን ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡
ከአርሶ አደሮቹ መካከል አቶ ደንቦቢ ሀንቆ፣ የአፈርና ውሀ ጥበቃ፣ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴና ሌሎች የግብርና ፓኬጆችን በአግባቡ መጠቀማቸው ለምርት መጨመር እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ምርቱን ለማሳደግ የተጠቀሙት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወጪ በመቀነስና የአፈር ለምነት በመጨመር ከሄክታር 32 ኩንታል የስንዴ ምርት አስገኝቶላቸዋል፡፡
ለተገኘው አመርቂ ውጤት ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ በግብርና ባለሙያዎች የተደረገላቸው ክትትልና ድጋፍም ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስታውሰዋል፡፡
አቶ ጎዳና በዴሳ በበኩላቸው፣ ለዘንድሮ የመኸር አዝመራ የተጠቀሙት ሙሉ የግብርና ፓኬጅ ምርታቸውን ከጠበቁት በላይ እንዳሳደገላቸው ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በኩታ ገጠም ካለሙት ሁለት ሄክታር መሬት ከ36 ኩንታል በላይ የጤፍ ምርት መሰብሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡
አርሶ አደር ኤዶ ጎበና በበኩላቸው 3 ሄክታር መሬታቸውን የስንዴና ጤፍ ሰብሎችን እያፈራረቁ በማልማት አመታትን አሳልፈዋል፡፡
የግብርና ስራቸው የተሻሻለ አሰራርን ያልተከተለ በመሆኑ ውጤቱም ዝቅተኛ፤ ኑሯቸውም ከእጅ ወደ አፍ እንደሆነ ያስታውሳሉ።
በግብርና ባለሙያዎች ምክርና እገዛ ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን በመጠቃማቸው ዘንድሮ ከአንድ ሄክታር 22 ኩንታል ጤፍ ማግኘታቸውን አውስተዋል።
የምዕራብ ጉጂ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ አያኖ አለማየሁ፤ በዞኑ ከ310 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር አዝመራ በዘር መሸፈኑን አስታውሰዋል፡፡
በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ከዚሁ መሬት ከ6 ሚሊዮን 800 ሺህ ኩንታል በላይ አጠቃላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ነው የተናገሩት።
እስካሁን ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የበቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍና ቦለቄን ጨምሮ የሌሎች ሰብሎች ምርት መሰብሰቡን አመልክተዋል፡፡
ከተሰበሰበው ምርት ውስጥ ከ985 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው የስንዴ ምርት መሆኑን ገልጸው ዘንድሮ ከዞኑ ለመሰብሰብ የታቀደው የሰብል ምርት ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ታሪኩ ብዛየሁ በበኩላቸው ሙሉ የግብርና ፓኬጅ የተገበሩ አርሶ አደሮች ምርት መጨመሩን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ፓኬጆቹ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም፣ ምርጥ ዘር፣ የኩታ ገጠምና የትራክተር አስተራረስ ዘዴ መተግበር ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡