የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

<p>ለሲሚንቶ ንግድና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች የወጡ መመሪያዎች ገበያውን ማረጋጋት ችለዋል-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር</p>

Feb 12, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ እምርታዊ ለውጥ ማምጣታቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ንግድና የሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሊቁ በነበሩ ለኢዜአ እንዳሉት፥ የሸቀጦችን ዋጋ በማረጋጋት የፍላጎትና አቅርቦት መጣጣም እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያውን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲወሰን በመደረጉ ባልተገባ መንገድ ለመበልጸግ ምርት በመሰወርና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር፣የዋጋ ንረት እንዲከሰት የማድረግ አዝማሚያዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ነገር ግን ሚኒስቴሩ ከፌዴራል እስከ ታችኛው እርከን ያለውን የንግድ መዋቅር በማነቃቃትና ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ውጤታማ ሥራ አከናውኗል ብለዋል፡፡

በዚህም ከሀምሌ 22/2016 እስከ ጥር 30/2017 ዓ.ም በተደረገ ክትትል ከ108 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶችና ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ አምራችና ሸማቾችን በማገናኘት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት የሚያስችሉ አንድ ሺህ 447 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ዋጋውን በማረጋጋት ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ ግብርና የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸው፥ ከዚህ ባለፈ በመመሪያ የተደገፈ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።

በሲሚንቶና ጨው ንግድ እንዲሁም በነዳጅ ግብይት ላይ የወጡ ሶስት የአሰራር ማሻሻያ መመሪያዎች ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሲሚንቶ ንግድ መመሪያ ቁጥር 960/2015 ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ እንደተሻሻለ ገልጸው፤ ሚኒስቴሩ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሚያወጣው እና ተጠቃሚው በሚገዛበት ዋጋ መካከል የተጋነነ ልዩነት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

መመሪያው በፋብሪካውና ተጠቃሚዎች መካከል ያለውን ያልተገባ የድለላ ሰንሰለት በማስቀረት የምርት እጥረቱን ከመፍታቱም ባለፈ፤ የገበያ ዋጋውን በከፍተኛ ሁኔታ ማውረድ ማስቻሉን ተናግረዋል።

የጨው ግብይት መመሪያ 1032/2017 ገበያውን መስፈርቱን አሟልተው ለገቡ ነጋዴዎች ክፍት በማድረግ ፍትሀዊ ውድድር እንዲሰፍን አድርጓል ብለዋል፡፡

መመሪያው የመጋዘን ክምችትን በማስቀረት አምራች ኢንዱስትሪዎች ለግብዓት የሚያስፈልጋቸውን ጨው ያለምንም ውጣ ውረድ እንዲያገኙት ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ምርቶች በሥፋት ወደ ገበያ እየቀረቡ መሆኑን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን ተከትለው በማይሰሩ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.