አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2017(ኢዜአ)፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ለተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መሰረት የጣለ እርምጃ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
ሪፎርሙ በየትኛውም መመዘኛ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ይገኛል ሲሉም ገዥው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም አዘጋጅነት በሚቀርበው ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” በተሰኘው ፕሮግራም ቀርበው በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ሂደትና ተስፋዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ብቸኛ የኢኮኖሚ ምንጭ የነበረው መንግስት ለህዝቡ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት የሚያወጣው ወጪ እንደነበር አውስተዋል።
የፕሮጀክት መረጣና አስተዳደር፣ ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ያላቸውን ብድሮች መበደር እና በጊዜው አለመመለስ በወቅቱ ይታዩ ከነበሩ ችግሮች እንደነበሩ ለአብነት ጠቅሰዋል።
ይህም የዕዳ ጫና፣ የፋይናንስ አለመረጋጋት፣ የግሉ ዘርፍ ምርታማነት ማነስ እና ከዋጋ ጋር የተያያዙ ጫና እና የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት መፍጠሩን አስታውሰዋል።
ለውጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወደ ስልጣን ሲመጡ መልከ ብዙ ችግሮችን የተሸከመ ኢኮኖሚ ነበር ብለዋል።
በዚህም የፖሊሲ እና ብዝሃ የኢኮኖሚ የዕድገት አማራጮችን መሰረት ያደረገ የአገር በቀል መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን አመልክተዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሪፎርም ጥሩ ጅማሮ የነበረው ቢሆንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአገር ውስጥ ግጭቶች፣ የዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የነበሩ ጫናዎች፣ የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት እና ሌሎች ችግሮች ኢኮኖሚያዊ ጫና ማሳደሩን ነው አቶ ማሞ ያወሱት።
ይሁንና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈተናዎች ውስጥ በማይበገር አቅም በመቀጠል ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አመልክተዋል።
የውጭ ዕዳ ከአገራዊ ጥቅል ምርት ጋር ያለውን ምጣኔ መቀነስ፣ የድጎማ ስርዓት ማዕቀፍ እርምጃዎች ውጤት ማመጣት፣ የግብርና ምርታማነት ዕድገትእና የሀብት መሰብሰብ አቅም ዕድገት ማሳያታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢኮኖሚው በግሉ ዘርፍ እንዲመራ ለማድረግ በተወሰዱ እርምጃዎች ለውጦች መምጣታችውን ገልጸዋል።
ከለውጡ በፊት 70 በመቶ ገደማ የባንኮች ብድር ወደ ለመንግስት ብቻ እንደነበረና አሁን ላይ ግን 80 በመቶ ገደማ የሚጠጋ ብድር ለግሉ ዘርፍ እየተሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ቴሌኮም፣ ሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መሆኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ ተወዳደሪነትን ከማሳደግ እና ኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ የራሱ ድርሻ መወጣቱን አብራርተዋል።
የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሁለተኛ ምዕራፍ ጥልቅ እና በርካታ ዘርፎች የያዘ ሁሉን አቀፍ እና ቅንጅታዊ መዋቅሩ ጠንካራ እንደሆነ አንስተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት እና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሰረት የጣለ ነው ብለዋል።
የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ ከመንግስት ቁጥጥር ወጥቶ ወደ ገበያ መር ስርዓት መግባቱ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት መጨመሩንና የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ማሳደጉን ጠቁመዋል።
በመደበኛ እና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ከሰባት በመቶ በታች ዝቅ በማድረግ ትይዩ ገበያውን አቅም ማዳከም መቻሉን ጠቅሰዋል።
ዘላቂ የዕዳ አስተዳደር እንዲኖር እየወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም ጤናማ የዕዳ አስተዳደር ለመፍጠር አስተዋጽኦ መድረጉን ጠቅሰዋል።
ጥብቅ የገንዘብ እና ፊሲካል ፖሊሲዎች ትግበራም ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ የራሱን ሚና መጫወቱን ነው ያስረዱት።
በማሻሻያው ዜጎች እንዳይጎዱ የደሞዝ ጭማሪና በመሰረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ድጎማዎችን ማድረግ ጨምሮ ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ታሪካዊ፣ አይነኬ የተባሉ ዘርፎች ላይ ድፍረት የተሞለባት ውሳኔ የተላለፉበት፣ የተቀናጀ፣ በጥናት እና በጥንቃቄ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።
ሪፎርሙ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍ አቅም በማሳደግ፣ የስራ እድል በመፍጠርና የገቢ መሰብሰብ አቅምን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ በሁሉም መመዘኛዎች ሪፎርሙ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ነው ብለዋል።
ሪፎርሙ በዘላቂነት ቀጣይነት ያለው ዕድገት በመፍጠር ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ውጤት እንደሚያመጣ አሁን ላይ ካሉ አመላካቾች በመነሳት መናገር ይቻላል ነው ያሉት።