አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2017(ኢዜአ)፦ የንብረት ታክስ አዋጅ የገቢ አቅምን በማሳደግ ህዝቡ ለሚያነሳቸው የልማትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የጎላ ሚና እንደሚኖረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባዔው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል።
አዋጁን አስመልክቶ በፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ያላቸውን ጥያቄ እና አስተያየት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ከሚመነጨው ሀብት አኳያ የሚሰበሰበው ገቢ በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል።
በታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ለጥቅል አገራዊ ምርት(ጂ ዲ ፒ) ያለው አስተዋጽኦ ከ7 በመቶ እንደማይበልጥ ጠቅሰው ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን አብራርተዋል።
አዋጁ የታክስ መሰረትን ለማስፋት፣ የመንግሥት መሰረተ ልማት አቅርቦት አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበር አጋዥ መሆኑን አመላክተዋል።
በተለይም አዋጁ ገቢን በማሳደግ ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የላቀ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ አዋጁ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ገቢ በመሰብሰብ ለመሰረተ-ልማቶች እና ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች ለማዋል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት አዋጁ ከህዝቡ የኑሮ ደረጃ እና የገቢ ምንጭን ጋር እንዴት ይሄዳል፣ የዋጋ ግመታ ለሌብነት የተጋለጠ አይሆንም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል።
ለታክስ ከፋዩ ተደራራቢ ጫና አይፈጥርም ወይ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሲባል ምን ማለት ነው የሚሉና ሌሎች ሀሳቦችን አንስተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ አዋጁ በሕዝቡ ላይ የተጋነነ ጫና እንደማይፈጥር እና ከታክስ የሚገኘው ገቢም ተመልሶ ህዝቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የዋጋ ግመታው በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንደሚከናወን የገለጹት ሰብሳቢው፤ መክፈል የሚችሉትን ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የታክሱ ክፍያ በጥናት ላይ ተመስርቶ እየጨመረ እንደሚሄድ በማንሳት፤ አዋጁ በከተሞች የሚተገበርና የቤቱም ግምትም በባለሙያ የሚከናወን ነው ብለዋል።