ነገሌ ቦረና/ቡሌ ሆራ፤ ጥር 12/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ እና ምሥራቅ ቦረና ዞኖች በዘንድሮው የበጋ ወቅት 137 ሺህ በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ በማልማት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች ገለፁ።
የምዕራብ ጉጂ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ከራ ዳዲ(ዶ/ር) እንዳሉት በዞናቸው በዘንድሮው የበጋ ወቅት 103 ሺህ 738 ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን በዘጠኝ ወረዳዎች ከ94 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።፡
ምርታማነቱን ለማሳደግም ከ94 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸው፤ 73 ሺህ 192 አልሚ አርሶ አደሮች ሙያዊ እገዛ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።
በዞኑ በበጋ ስንዴ ልማት ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም እንዲሁ፡፡
የምስራቅ ቦረና ዞን ግብርና ፅህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ቦነያ ጎሎ በበኩላቸው እንዳሉት ምሥራቅ ቦረና ከክልሉ ዝናብ አጠር አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ገልፀው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በስንዴ ሰብል ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተያዘው የበጋ ወቅት 33 ሺህ 440 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ በስንዴ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ20 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በስንዴ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
በልማቱ በመሳተፍ ላይ ላሉ 20 ሺህ 816 አርሶ አደሮች የቀረበ 1 ሺህ 248 ኩንታል ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸው፤ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው አርሶ አደሮች መካከል በምዕራብ ጉጂ ዞን የቀርጫ ወረዳ ነዋሪ አቶ ገመቹ ባቲ እና አዶላ በራቆ የመስኖ የሰብል ልማቱ እምብዛም የተለመደ ባለመሆኑ ዝናብ ጠብቀው በሚያለሙት ሰብል ከእጅ ወደ አፍ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት እየተለመደና ባህል እየሆነ መጣቱን ገልጸው፤ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር በኩታ ገጠም የበጋ መስኖ ስንዴ እያለሙ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡