መቐለ ጥር 13/2017 ዓም (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩትና የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የበለስ ተክል በሽታን የመቋቋም አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የምርምር ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት የአዝርዕት ጥበቃ ተመራማሪ ዶክተር ተስፋይ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ከ350 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበለስ ተክል የተሸፈነ ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ተክሉ ''ኮቺንያል'' ተብሎ በሚጠራ በሽታ በመጠቃቱ የሚፈለገውን ያህል ፍሬ እየሰጠ አለመሆኑን ገልፀዋል።
በመቐለ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተማራማሪ ዶክተር ኪሮስ መለሰ በበኩላቸው፤ የበለስ ተክልን በሽታ የመቋቋም አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ የምርምር፣ የማባዛትና የማዳቀል ስራዎች በዩኒቨርስቲው፣ በእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩትና በባዮ ቴክኖሎጂ ማዕከል እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ተክሉን ከማከም ጎን ለጎንም ድርቅን ተቋቁሞ ብዙ ምርት እንዲሰጥ ለማስቻል 35 ዓይነት ዝርያዎችን በማዳቀል የተሻለው ተመርጦ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እየተሞከረ መሆኑን ዶክተር ኪሮስ ጨምረው ገልጸዋል።
እንዲሁም በሁለቱም ተቋማት ምርምር የተገኘው የበሽታው መከላከያ መድኃኒትም ውጤታማ መሆኑን በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በተግባር በመረጋገጡ የስርጭት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሰውና ለእንስሳት ምግብነት ይውል የነበረ ግማሽ ሄክታር የበለስ ተክል ''ኮቺኒያል'' በተባለ ተባይ ምክንያት መጎዳቱን የገለፁት ደግሞ በትግራይ ጋንታ አፈሹም ወረዳ ፋፂ ገጠር ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር የማነ ሀፍቱ ናቸው።
''የበለስ ተክልን በተሻለ ዝርያ ለመተካት እየተከናወነ ያለው በተግባር የተደገፈ ምርምር ተስፋ ሰጪ መሆኑን ማረጋገጥ በመቻላችን ተግባሩ በፍጥነት ሊጎለብት ይገባል።'' ብለዋል።
በክልሉ ፃእዳ እምባ ወረዳ ማይመገልታ ገጠር መንደር ነዋሪዋ ወይዘሮ ስላስ ንገሰ በበኩላቸው፤ ለምግብነት ከማዋል ባለፈ ፍሬውን በመሸጥ ተጨማሪ ገቢን ሲያገኙበት የነበረው የበለስ ፍሬ በበሽታ በመጠቃቱ የፈለጉትን ያህል ምርት ሊያገኙ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
''ተክሉ መልሶ እንዲለማና ፍሬ እንዲሰጥ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል'' ብለዋል።