አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮ-ኢንጂነሪግ ግሩፕ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀሉ ድርጅቱ ይበልጥ ትርፋማ እንዲሆን መልካም ዕድል እንደሚያመጣለት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ገለፁ።
የኢትዮ-ኢንጂነሪግ ግሩፕ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከተቀላቀሉ ስምንት የመንግስት ልማት ድርጅቶች አንዱ ነው።
በ2002 ዓ.ም ብረታ ብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) በሚል ይታወቅ የነበረው ይህ ተቋም በ2013 ዓ.ም በተሰራው ሪፎርም ኢትዮ-ኢንጂነሪግ ግሩፕ በሚል ስያሜ ዳግም መደራጀቱ ይታወሳል።
የኢትዮ-ኢንጂነሪግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኩባንያው ከተቆጣጣሪነት ወጥቶ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀሉ መልካም ዕድል ነው ብለዋል።
ይህም በቀጣይነት ያሉበትን ተግዳሮቶች እየቀረፈ ይበልጥ ትርፋማ ድርጅት ለመሆን ያግዘዋል የሚል እምነት አላቸው።
የኢትዮ-ኢንጂነሪግ ግሩፕ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከሚያድኑ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ወሳኝ ድርሻ ይዟል።
ግሩፑ እስካሁን 35 ፋብሪካዎችን ያላቸው ዘጠኝ አምራች ኢንዱስትሪዎች የመደገፍ፣ የመከታተልና የግብዓት ችግሮችን በመሙላት የተቆጣጣሪነት ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።
ፋብሪካዎቹ እንደ ብረት፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ታወሮች፣ የእርሻ ተሽከርካሪዎችና ፕላስቲክና መሰል ተኪ ምርቶችን የሚያመርቱ እንደሆኑ አንስተዋል።
ከተኪ ምርቶች ባሻገርም በቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በዚህም ግሩፑ በ2013 ዓ. ም አሁን የያዘውን ስያሜ ይዞ ዳግም ከተቋቋመ በኋላ ከኪሳራ ወደ ትርፋማነት እየተሸጋገረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማሳካቱን ጠቁመዋል፡፡