አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017 (ኢዜአ):- ባለፉት ሦስት ዓመታት በቤት ልማት ፕሮግራም 1 ሚሊዮን 500 ሺህ ቤቶች መገንባታቸውን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
ለውጡን ተከትሎ በተሰሩ ሥራዎች በመሰረተ ልማት አቅርቦት ዘርፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ ከፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ በኋላ በመሰረተ ልማት ዘርፍ በተቀመጡ አቅጣጫዎች በተከናወኑ ተግባራት እና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው ከ1996 እስከ 2012 ዓ.ም 380 ሺህ ቤቶች ብቻ መገንባታቸውን አስታውሰው፤ ከለውጡ በኋላ በቤት ልማት ፕሮግራም ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የቤትልማት ፕሮግራሙ በህብረት ሥራ ማህበራትና በሪል ስቴት ጭምር የግልና የመንግሥት አጋርነት መርሃ ግብሮችን በመንደፍ መከናወኑንም አብራርተዋል።
በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ 1 ሚሊዮን 500 ሺህ ቤቶችን መገንባት ተችሏል ብለዋል።
ከተያዘው እቅድ አኳያ የተገኘው ውጤት አበረታች ቢሆንም ካለው የህዝብ ፍላጎት አንፃር የበለጠ መሥራት የሚጠይቅ ይሆናልም ነው ያሉት።
በኮሪደር ልማትም ከደረጃ በታች ሆነው የተገነቡ አካባቢዎችን በጥራት በመገንባት እንዲሁም ለመኖሪያ ምቹ አካባቢዎችን በመፍጠር ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በከተሞች 74 በመቶ ግንባታዎች ከደረጃ በታች መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ የኮሪደር ልማት ስራው የከተሞችን ጥራትና ደረጃ እያሻሻለ ይገኛል ነው ያሉት።
ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው የመንገድ ልማት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተው ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 18 ሺህ 790 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ መገንባቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የመንገድ ሽፋኑ 171 ሺህ 174 ኪሎ ሜትር መድረሱንም ነው የተናገሩት።
በከተሞች የአገለግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ድጅታላይዝ በማድረግ እንዲሁም ልማታዊ የምግብ ዋስትን በማረጋገጥ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።