ደብረ ብርሀን ፤ ጥር 21/2017 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወጣቱን ለፈጣን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ብቁና ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑ ተገለጸ።
በሰሜን ሸዋ ዞን የኢትዮ ኮደርስ የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ ተግባራት ላይ የመከረ መድረክ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄዷል።
የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሙሉነህ ዘነበ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ፤ በክልሉ በ22 ከተሞች የኢትዮ ኮደርስ መርሃ ግብር እየተተገበረ መሆኑን አመልክተዋል።
ስልጠናው የነገይቱን ኢትዮጵያን የሚረከቡ ወጣቶችን ለማዘጋጀት ያለመ መሆኑንና ለዚህም የክልሉ መንግስት በወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ስራና ስልጠና መምሪያ ምክትል ሀላፊ ነፃነት ንጉሴ በበኩላቸው፤ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ የዳበረ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመገንባት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከ14 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች በመርሀ ግብሩ ዙሪያ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ 3 ሺህ 92 የሚሆኑት ስልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉን አስረድተዋል።
ክእነዚህም 2 ሺህ 153 የሚሆኑት ስልጠናውን በብቃት አጠናቀው ዓለም አቀፍ ሰርተፍኬት መውሰድ ችለዋል ነው ያሉት።
የኮደርስ ስልጠና በተለይ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ ስልጠናው በስፋት እንዲሰጥ እንሰራለን ሲሉ አስታውቀዋል።
ስልጠናው በዞኑ 56 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ የ11ኛ እና 12 ክፍል ተማሪዎች እየተሰጠ ነው ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ፀጋዬ እንግዳ ወርቅ ናቸው።
የደብረብርሀን መምህራን ኮሌጅ ተወካይ አቶ ቻለው አሳሳ በበኩላቸው፤ ለኮሌጁ ተማሪዎችና መምህራን ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ 44 የሚሆኑት ስልጠናውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ስልጠናውን በስፋት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።