አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የጤና ልማት ስራዎችን ምርምር ላይ ተመስርቶ እያከናወነ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ገለጹ።
በጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሳይንሳዊ ምርምር በማስደገፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በባህላዊ መድሀኒት ጥናት ላይ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተመራማሪዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች የህዝቡን የጤና ችግሮች መፍታት የሚችሉበትን እድል መፍጠር ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ካሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር በጤና ልማት ስራ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስራ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ያሉንን ጸጋዎች በመለየት እና ምርምር በማካሔድ በዘርፉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ የተጣለበትን ሀገራዊ ሀላፊነት በብቃት መወጣት የሚችል መሆኑን ጠቁመው የጤና ልማት ስራዎችን በምርምር ላይ ተመስርቶ እያከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
ምርምርን ከልማት እንዲሁም የጤና የፈጠራ ስራዎችን ከትግበራ ጋር በማቀናጀት እየተሰራ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።
በዚህም የመድሀኒት፣ የክትባት፣ የህክምና እና የምርመራ መሳሪያዎች ልማትን እና ኢንዱስትሪን እንዲደግፉ በማድረግ ረገድ ተቋሙ የተጣለበት ኃላፊነት የላቀ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከጤና ቢሮ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ በትብብር ሲሰራ መቆየቱንና በዘርፉ የሚካሔደውን የጤና ልማት ስራ ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉን የጤና ልማት የትኩረት መስኮች መለየት እና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በሳይንሳዊ ምርምር መፍታት የሚቻልበትን ስርዓት ማጠናከር እንደሚገባ መጠቆማቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ኢንስቲትዩቱ በጤና ምርምር፣ በፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰው ሀብት ልማት፣ በኢንዱስትሪ ልማት እና በሌሎች ዘርፎችም በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የዘርፉ ተመራማሪዎች በክልሉ በጤናው ዘርፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መስራት የሚችሉበት ስርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።
የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው በጤናው ዘርፍ የሚካሔደውን ሁሉ አቀፍ ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የእውቀት ሽግግር እና ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ መሰረታዊ የሆኑ የጤና ችግሮችን በመለየት ጥናትና ምርምር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ባህላዊ መድሀኒቶች በዘመናዊ ህክምና ላይ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ማመላከት ይገባል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ የክልል ከፍተኛ የስራ ኅላፊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ከወራቤ፣ ከወልቂጤ እና ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።