የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

<p>ህብረት ስራ ማህበራት ይበልጥ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)</p>

Feb 6, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2017(ኢዜአ)፡-ህብረት ስራ ማህበራት ይበልጥ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽንና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኮሚሽን ትብብር "የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ ሲምፖዚየም ተካሒዷል፡፡


በሲምፖዚየሙ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፣ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤና የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጰያ ባለፉት የለውጥ አመታት በርካታ ተግዳሮቶችን በማለፍ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግባለች ብለዋል፡፡

ህብረት ስራ ማህበራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

በተለይ ለግብርና ክፍለ ኢኮኖሚው ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂ በማስፋትና እሴት በመጨመር እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ማህበራቱ የልማት አጋርነታቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ ህብረት ስራ ማህበራት በአገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ የአሰራር ስርዓታቸውን በማዘመንና የህግ ማዕቀፍ በማበጀት አገልግሎት አሰጣጣቸው የተሳለጠ እንዲሆን እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በተለይ በቅርቡ የተደረገው ሪፎርም አሰራራቸውን በማሻሻል አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።

የህብረት ስራ ማህበራት ትብብርን በማጎልበት ለጋራ እድገት በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ ተናግረዋል፡፡

ተለዋዋጭ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ክስተቶችን በመሻገር አዳዲስ መፍትሔዎችን ለማምጣት ህብረት ስራ ማህበራት ከመቸውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ናቸው ብለዋል፡፡

ማህበራቱ ፍትሃዊ ግብይትን እንዲያሰፍኑ፣ የግብርና ምርታማነትን እንዲያሳድጉና የምርት እሴት ሰንሰለትን እንዲያጠናክሩ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይ፤ በኤግዚቢሽኑ፣ ባዛሩና ሲምፖዚየሙ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ማህበራት ይሳተፋሉ ብለዋል።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ የህብረት ስራ ማህበራት የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት መድረክ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

በኢግዚቢሽንና ባዛሩ ከ350 በላይ የግብርናና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም ከመቶ በላይ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደሚሳተፉበትና ከ110 በላይ የተለያዩ ምርቶች እንደሚቀርቡበት ተገልጿል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄደው ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ በአዲስ አበባ ደረጃ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ መዘጋጀቱ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.