አዳማ፤ ጥር 28/2017(ኢዜአ)፦ የሎጂስቲክስ ዘርፉ የአገር ኢኮኖሚን መደገፍ እንዲችል የአፈጻጸምና የአደረጃጀት ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስቴሩ ለሁሉም ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሎጂስቲክስ አመራር አባላትና ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው የስልጠና መድረክ ማምሻውን ተጠናቋል።
ሚኒስትሩ በማጠቃለያው ላይ እንደገለጹት የሎጂስቲክስ ዘርፉ በመሰረተ ልማት እጥረት፣ ህገ ወጥ የኬላዎች መበራከት፣ በጭነት ተሽከርካሪዎች ቁጥር ማነስና በሌሎች ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ አልሆነም።
የሎጂስቲክስ ዘርፉ የአገር ኢኮኖሚን መደገፍ እንዲችል የአፈጻጸምና የአደረጃጀት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሎች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተው ይህ ስልጠናም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ አስረድተዋል።
በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በሚኒስቴሩ ሎጂስቲክስና መሠረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዴንጌ ቦሩ በበኩላቸው እንደ ሀገር የሎጂስቲክስ አፈጻጸም እንዲሻሻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም ያልተቆጠበ ተሳትፎና ጥረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።