የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

<p>የተፋሰስ ልማት ስራው ምርታማነታችንን እያሳደገልን ነው - አርሶ አደሮች</p>

Feb 7, 2025

IDOPRESS

ሮቤ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፡- ባለፉት ዓመታት ያከናወኗቸው የተፋሰስ ልማት ስራዎች ምርታማነታቸውን እያሳደገላቸው መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የባሌ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት በበኩሉ በዞኑ 105 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ 320 ተፋሰሶች ተለይተው በዘንድሮው የበጋ ወራት እየለሙ መሆኑን ገልጿል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የዞኑ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ሁሴን በከር በሰጡት አስተያየት በቀደሙት ዓመታት መሬታቸው በጎርፍ በመሸርሸሩ ምርታቸው መቀነሱን አስታውሰዋል።

ችግሩን ለመፍታትም የአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ ወጥቶ በቅንጅት ያከናወናቸው የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማት ስራዎች የተራቆተ መሬታቸው ለምነቱ እንዲመለስ አግዟል።

በዚህም ከግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ የሚያገኙት ምርት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

አርሶ አደር አብዱረህማን ማህሙድ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በበጋ ወቅት ደርቀው የነበሩ ምንጮች ጎልብተው ዓመቱን ሙሉ እንዲፈሱ ማድረጉን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ ለግብርናም ሆነ ለእንስሳት ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር አወንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው ያነሱት።

የተፋሰስ ልማት ስራዎቹ ባስገኙት ፋይዳም የአካባቢያቸው ማህበረሰብ በየዓመቱ በነቂስ ወጥቶ የመስራት ፍላጎቱ እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።

የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራው በተለይም የጎርፍና የአፈር መከላትን በማስቀረቱ ተመናምኖ የነበረው የተፈጥሮ ደን እያገገመ በመምጣቱ ለግብርና ሥራችን እያገዘን ነው ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ቃሲም ሲራጅ ናቸው።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዳዲ በበኩላቸው በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ስራዎች ከ320 የሚበልጡ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረጉ ስራዎች እየለሙ ናቸው፡፡

በዚህም በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዳ 20 ሺህ ሄክታር መሬት ከንክኪ ነፃ ከማድረግ ባለፈ 87ሺህ እርከኖችና ሌሎች የተለያዩ የተቀናጁ ስራዎች አንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ለሁለት ወራት በዘመቻ በሚካሄደው የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማት ሥራ 105 ሺህ ሄክታር መሬትን የሚያካልል ሥራ እንደሚከናወን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.