አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2017(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን አስተዋፅዖ ወሳኝ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት፣ ስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወር የዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።
በሪፖርቱ የቀረበው ዕቅድ አፈፃፀም የተሻለ ጥንካሬዎች የታዩበት መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል።
በተጨማሪም በእጥረትና ትኩረት ይሻሉ ያላቸው ጉዳዮችን በቀጣይ በመስራት አፈፃፀማቸውን ማሻሻል እንደሚገባም አመላክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሬ ሌንጮ(ዶ/ር) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መንግስት የያዘውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ከድህነት ለመውጣትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ ጠቁመው ተቋሙ ታዳጊ ወጣቶችን ለማበረታታት የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከአመራር አንፃር የተነሱ አንዳንድ ቅሬታዎችን በሚመለከት ስብጥሩን የጠበቀ፣ ከጥገኝነት ነፃ እና እውነትን መሰረት በማድረግ የሚሰራ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በማቋቋም መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በሪፖርቱ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሳ ሲሆን የሚንስቴሩ የስራ ሀላፊዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለማሻሻል ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከኢኖቬሽን አንፃር የተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችን አካታች በማደረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም አብራርተዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተቋማትን ከማገዝ እና እሴቶችን ከማበልፀግ አንፃር ግብርናን እና ጤናን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎችን በማካተት በርካታ ሰራዎች እየተሰሩ መሆኑን ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።