ጂንካ፤ ጥር 29/2017(ኢዜአ)፡- ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን በጥናትና ምርምር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
አቶ አገኘሁ ተሻገር እና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የዩኒቨርሲቲውን የስድስት ወራት አፈፃፀም ገምግመዋል።
አቶ አገኘሁ በዚህን ጊዜ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታት ቢሆነውም ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን የአካባቢው ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል።
ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ሥራዎቹ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በተለይ በአካባቢው ያለውን የእንስሳት ሀብት ዝርያ በማሻሻል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማጠናከር ማህበረሰቡን እንዲያግዙም አስገንዝበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ኩሴ ጉድሼ(ዶ/ር) በበኩላቸው ከሥራ አመራር ቦርድ አባላት ጋር በተካሄደው ግምገማ የተነሱ የአፈጻጸም ክፍተቶችን በመሙላት ጥናካሬዎችን በማስቀጠል ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ተግተን እንሰራለን ብለዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የአካባቢው አመራር አባላትና የማህበረሰብ ተወካዮች ታድመዋል።