አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- ጨፌ ኦሮሚያ ለአባላቱና ለህብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ በይፋ አስጀምሯል።
መተግበሪያው ጨፌው ለአባላቱ ወቅታዊ መረጃዎችን ለመስጠት እንዲሁም በጊዜና በቦታ ያልተገደቡ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጠናከር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑም ተጠቁሟል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን፣ የጨፌው አባላትን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
አፈ-ጉባኤዋ ሰዓዳ አብዱራህማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሞባይል መተግበሪያው የጨፌው አባላት የሕዝብ ውክልና ስራቸውን በቀላሉ እንዲወጡ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የጨፌው አባላት የጉባኤ አጀንዳዎችን፣ በጨፌው የተላለፉ ውሳኔዎችን ብሎም የተለያዩ መረጃዎችን በጊዜ እና በቦታ ሳይገደቡ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የሞባይል መተግበሪያው የወረቀት አሰራሮችን የሚያስቀር እና ዲጂታል አሰራሮችን ከማስፋፋት አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
መተግበሪያው በዋናነት አምስት ትልልቅ መነሻዎችን(menu) የያዘ ሲሆን ሕጎች፣ ቀን መቁጠሪያ፣ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ የጨፌውን አባላት ስም ዝርዝር እና የቋሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም ሴቲንግ ያለው መሆኑም ተጠቁሟል።
ጨፌው የሞባይል መተግበሪያውን ከኔዘርላንድስ ኢንስቲትዩት ፎር መልቲፓርቲ ዲሞክራሲ ተቋም ጋር በመተባበር ያበለጸገ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውልም ተጠቁሟል።