አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ለቀጣዩ ትውልድ መደላድልን መፍጠር የብልጽግና ፓርቲ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ነው ሲሉ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔውን ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ያካሄደ ሲሆን፤ በተለያዩ ዘርፎች የተገኙ ስኬቶችን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በኢኮኖሚ መስክም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የፓርቲው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑ ተመላክቷል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፤ በፓርቲው አመራር ሰጪነት ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ በማዕድንና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ ሁሉን አቀፍ እድገት ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥሉ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ብዝሃ ኢኮኖሚ ሥርዓት መዘርጋት ተችሏል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህም የዜጎችን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉ ውጤቶች ተገኝተዋል ነው ያሉት።
በግብርናው ዘርፍም በምግብ ራስን ለመቻል በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው፤ የራስ ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ መጀመሩ ትልቅ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መርሃ ግብርም የአምራች ዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ መቻሉ ተጠቃሽ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ከብልጽግና ፓርቲ መጀመሪያው ጉባዔ በፊት በዲጂታል ሲንቀሳቀስ የነበረው በሚሊዮን የሚቆጠር ኃብት በአሁኑ ወቅት በትርሊየን ወደሚቆጠር ማደጉን ጠቁመው ይህም የለውጥ እሳቤዎች ትግበራ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ለቀጣይ ትውልድ መደላድልን መፍጠርም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደሀገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም ከቴክኖሎጂ፣ ከአደረጃጀትና ገበያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ የበለጠ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የተገኙ ስኬቶችን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ መሆኑን ገልጸው፤ ግቦቹ ስኬታማ እንዲሆኑ የባለ ድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።