የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

<p>በሐረር ከተማ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የስራ ባህልን ቀይረዋል</p>

Feb 12, 2025

IDOPRESS

ሐረር ፣የካቲት 4/2017 (ኢዜአ) ፡-በሐረር ከተማ በሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የስራ እድል ከማግኘታቸው ባሻገር የስራ ባህላቸው መቀየሩን በልማቱ የተሰማሩ ዜጎች ተናገሩ።

በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ፍጥነትና ጥራትን ጠብቀው እየተከናወኑ ስለመሆኑም ተገልጿል።

በከተማው በአባዲር ፕላዛ የኮሪደር ልማት ስራ በግንበኝነት የተሰማሩት አቶ ደሳለኝ መንግስቴ እንደሚናገሩት፤ በክልሉ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የክልሉን ገጽታ እየለወጡ ናቸው።

በከተማው የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረጉ ባለፈ "አዳዲስ የስራ ባህልና ሙያዊ ክህሎትን እንድናገኝ አስችሎናል" ብለዋል።


በጥርብ ድንጋይና በቅርፃቅርጽ ስራ የተሰማራው ወጣት ፈቀደ መንግስቱ እንደሚገልጸው በከተማው በሚከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ እሱን ጨምሩ በስሩ ለሚገኙ 14 ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል።

የኮሪደር ልማት ስራው ቀደም ሲል "በውስን ሰዓት የምናከናውነውን ስራ በምሽትና በሌሊት በማከናወን የምናገኘው ገቢ እንዲያድግ አድርጓል" ብሏል።


የኮሪደር ልማት ስራው የከተማዋን ልማት ከማፋጠን ባለፈ በስሩ ለሚገኙ 40 ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር "እኔና ወጣቶቹ ከራሳችን አልፈን ቤተሰቦቻችንን እንድንረዳ ያስቻለ ነው" ያሉት ደግሞ በተቋራጭነት የተሰማሩት አቶ ይትባረክ ተመስገን ናቸው።

በተለይም በስራው ላይ የሚመጡ አዳዲስ አሰራሮች "ክህሎት እንድናገኝና የተሻለ ስራ እንድናከናውን አስችሎናል" ሲሉም ተናግረዋል።


በከተማው የአባዲር ፕላዛ የአረንጓዴ ስፍራ የኮሪደር ልማት ግንባታ ስራን የሚያከናውነው የክልሉ የኮንስትራክሽንና መሰረተ ልማት ስራዎች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፈቲህ ረመዳን በበኩላቸው በጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ ዙርያ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ 1 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት የሚሸፍን መሆኑን ጠቅሰዋል።

ታህሳስ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በተጀመረው ስራም የአረንጓዴ ልማት፣ የመናፈሻ፣ የአንፊ ትያትር፣ የጀጎል ዓለም ዓቀፍ ቅርስን የመጠበቅና ሌሎች የኮሪደር ልማት ሰራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በስራውም 120 ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.