አዲስ አበባ፤የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፦ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የፋይዳ አገልግሎቶችን አጠቃሎ የያዘ የፋይዳ መተግበሪያ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
መተግበሪያው በተቋሙ ባለሙያዎች እንዲለማ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን በአንድሮይድ እና በኣይ ኦ ኤስ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች በዛሬው እለት ለዜጎች ይፋ ተደርጓል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን አማካሪ አቤኔዘር ፈለቀ፥ ይፋ የተደረገው መተግበሪያ የተለያዩ ሙከራዎች እና የደህንነት ማረጋገጫ የተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።
ይፋ የተደረገው የሞባይል መተግበሪያ ህብረተሰቡ የሚያገኛቸውን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ በተደገፈና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል።
መተግበሪያው ዜጎች የጠፋባቸውን ወይም ያልደረሳቸውን የፋይዳ ቁጥር ዳግም ለማግኘት፣የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን በካርድ መልክ አሳትሞ ለመያዝና የካርድ ህትመት ለመጠየቅ ያስችላል።
ከዚህ በተጨማሪ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለማግኘት በሚመለከተው አካል ሲመዘገቡ የተሳሳተባቸው መረጃ ካለ በስልካቸው ላይ መረጃውን ማስተካከል የሚችሉበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው።