የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፡-የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡታጅራ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ጎበኙ፡፡
በቡታጅራ ከተማ በሁለት ምዕራፍ የሚጠናቀቅ የ25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ የ17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የልማት ስራ በፍጥነትና በጥራት በመሰራት ላይ ይገኛል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሙስጠፋ ሀሰን፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ውብ ከማድረግ ባለፈ ለንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተመራጭ ለማድረግ የሚያስችል ስራ መሆኑን ለጎብኝዎቹ አብራርተዋል።
የከተማዋን የኮሪደር ልማት በእቅዱ መሰረት በጥራትና በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በጉብኝቱ ላይ ከሚንስትሩ በተጨማሪ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች ጭምር የኮሪደር ልማት በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።