ደሴ፤ የካቲት 8/2017(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ የሚስማር ፋብሪካ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተመርቆ ወደ ምርት ገብቷል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው፤ ሰላም በማስጠበቅ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጠሉ በመደረጉ በርካታ ፋብሪካዎች ተገንብተው ወደ ምርት እየገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዕለቱ የተመረቀው ፋብሪካም በክልሉ የግንባታ ዘርፍ ግብዓት በማቅረብ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ አለባቸው ሰይድ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ስምንት ፋብሪካዎቹ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን አስታውሰዋል።
ተኪ ምርት ላይ የተሰማሩት ፋብሪካዎቹ ገበያ የማረጋጋትና የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ሚናቸውን ጠቅሰው፤ የተመረቀው ሚስማር ፋብሪካም ለግንባታ ዘርፉ መነቃቃት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የፋብሪካው ባለቤት አቶ ካሳሁን ፍቅሬ ፋብሪካውን ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ አሁን ላይ በቀን አምስት ቶን ሚስማር እያመረተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን እስከ 20 ቶን ሚስማር እንደሚያመርት ጠቅሰው፤ እስካሁን ለ58 ዜጎች የስራ ድል ፈጥሯል ብለዋል።