ባህርዳር ፤ደሴ የካቲት 10/2017 – በአማራ ክልል በተያዘው የበጋ ወራት ከ307 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እስካሁን በመስኖ ማልማት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ከዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊዎችና ቡድን መሪዎች ጋር የ2017 ዓ.ም የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በባህር ዳርና ደሴ ከተሞች ዛሬ አካሂዷል።
በደሴ በተካሄደ መድረክ ላይ የተገኙት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደገለጹት በተያዘው የበጋ ወራት እስካሁን ከ307 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት ተችሏል።
ይህም በመኸር ልማት ከሚገኘው ምርት በተጨማሪ በመስኖ ልማት አርሶ አደሩን በማሳተፍ በምግብ ራሱን ከማስቻል ባሻገር ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለገበያ የሚተርፍ ምርት እንዲገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተያዘው የበጋ ወራት ከ340 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን ከለማው ከ307 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥም 191 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በበጋ ስንዴ የተሸፈነ ነው ብለዋል።
በባህርዳርና ኮምበልቻ ከተሞች በተካሄዱት መድረኮች የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።