አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2017(ኢዜአ)፦ የባህርዳር ኮሪደር ልማት ተፈጥሯዊ ውበቷን ይበልጥ በመግለጥ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ከተማ ያደርጋታል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ልማት አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዶክተር አሕመዲን በባህርዳር ከተማ አመራሮች መሪነት ከክልሉ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የኮሪደርና የጣና ዳር ልማት ስራዎችን የሳይት ምልከታ ማድረጋቸውን ገልጽዋል።
በዚህም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ዘመኑን የዋጁ፣ ሁሉም የከተማው ነዋሪ ህብረተሰብ በእኩልነት የሚጠቀምባቸው ናቸው ማለታቸውን ከአማራ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በተለያዩ ነገሮች ተጋርዶ የነበረውን የጣና ሀይቅና ዳርቻ በመክፈት ለነዋሪዎችና ጎብኝዎች እይታ በመግለጥ ሀይቁን ከመንገዱና ከከተማው ጋር የማስተሳሰር ስራ መከናወኑንም ጠቁመዋል።
በኮሪደር ልማቱ የውበትና አረንጓዴ ቦታዎች ልማት፣ የመዝናኛና ማረፊያ ቦታዎች፣ ፋውንቴን፣ መፀዳጃ ቦታዎች፣ የግራ ቀኝ የብስክሌት መንገድና ህዝብ እንደልብ የሚንቀሳቀስበት ዘመናዊ የእግረኞች መንገድ በልዩ ሁኔታ ያካተተ መሆኑን መመልከታቸውንም ነው ያስታወቁት፡፡
በቀንና በምሽት እየተከናወነ ያለውን ስራ እያስተባበሩ የሚገኙ የከተማው አመራሮችንና ባለሙያዎችን እንዲሁም በፕሮጀክቱ እየተሳተፋ ያሉ አካላትንም ማበረታታታቸው ተገልጿል።
እንደዚህ አይነት የድጋፍና ክትትል ተግባር በቢሮውና በሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ዶክተር አሕመዲን መናገራቸውም በመረጃው ተመላክቷል፡፡