ሰመራ፤ የካቲት 11/2017 (ኢዜአ)፡- የጋራ አረዳድን በማስረፅ ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር እና ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ።
"ብሔራዊ ጥቅሞቻችንና ቀጠናዊ ትስስር ለሚዛናዊ የህዝቦች ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሐሳብ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
የውይይት መድረኩን የከፈቱት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሠላምና የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ውበቴ ታደገ እንዳሉት፤ "ዘላቂ ሰላም እና አገራዊ መረጋጋት ሊኖር የሚችለው በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤ ሲኖር ነው"።
እንደ አገር እና ዜጋ የጋራ የሆኑ ህልሞች፣ መገለጫዎች፣ ስጋቶች፣ ጥቅሞችና እሴቶች ያሉን ህዝቦች በመሆናችን የጋራ አረዳድን በማዳበር ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ ማስረፅ አለብን ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን ያስገነዘቡት ወይዘሮ ውበቴ፤ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛውን ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር በመሥራት በጋራ ለመልማትና ለማደግ እየሠራች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ቀጠናዊ ትስስርን በማጎልበት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለውም አብራርተዋል።
በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱራህማን ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው በመድረኩ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅሞች ማስጠበቅና ማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ይመከራል ብለዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይም በሠላም ሚኒስቴር የብሔራዊ መግባባት ዴስክ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ጥላሁንን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና ተማሪዎች እንዲሁም እንግዶች ታድመዋል።