አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገች ባለው ጉዞዋ የስንዴን ምርትን እንደ ቁልፍ ምሰሶ በመጠቀም በጀመረችው ስራ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገች ያለውን ጥረት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ምርታማነት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በዘለለ በረጅም ጊዜ ራስን ለመቻል ጠንካራ የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰዱን አመልክቷል።
የተጀመሩ ጥረቶች ኢትዮጵያ ከተረጂነት ተላቃ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ ያላትን መሻትና ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጿል።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የፖሊሲ ግብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እና ህዝቧቹ የህልውና ጉዳይ ነው ብሏል ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው።
ኢትዮጵያ ስንዴን በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገች ባለው ጉዞዋ ውስጥ እንደ ቁልፍ ምሰሶ በመጠቀም በጀመረችው ስራ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሏን ጠቅሷል።
የግብርና ምርትን ለማሳደግ መንግስት በስፋት ከወሰደው አማራጭ አንዱና ዋናው ኢኒሼቲቭ የመስኖ ግብርና እንቅስቃሴን ማሳደግ በመሆኑ ውጤቱ በጉልህ እየታየ ነው።
ለዘመናዊ ግብርና የሚያገለግሉ ማሽኖችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ከማድረግ ጀምሮ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።
በዚህ መነሻነትም እ.አ.አ በ2022/23 የምርት ዘመን 151 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ስንዴ አምርታለች። ከዚህ ውስጥ 104 ሚሊዮን ኩንታል በመኸር እና 47 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በበጋ መስኖ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል።
በቀጣዩ ዓመት እ.አ.አ በ2023/24 ደግሞ 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማምረቷንና በመኸር 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን እና 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን ደግሞ በበጋ መስኖ በመሰብሰብ ከፍተኛ እመርታ ማሳየቷን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።
ይህ አሃዝ የሚያሳየው ኢትዮጵያ በግብርና ምርት ላይ የምታሳየው እመርታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተሻሻለ መሆኑን ነው።
በመስኖ ላይ የተመሰረተ ግብርና፣ የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች፣ የግብርና ዘርፍ ማበረታቻዎች፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የግብርና ምርቶች ክላስተሮች እና አገልግሎቶች የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር ትልቅ ሚና እንደተወጡ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የግብርና ናሙና ቆጠራ፣ አስተዳደራዊ መረጃዎች ፣ የመስክ ጥናቶች እና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለረጅም ጊዜ ተአማኒነት ያላቸው ቁጥራዊ መረጃዎችን የማውጣት ልምድ እንዳለ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ በምግብ እራስን የመቻል አጀንዳ ከብሔራዊ የትኩረት አቅጣጫነት ባለፈ የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አቅም ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
አጀንዳው የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚችሉ የሚያሳይ መሆኑንም እንዲሁ።
በምግብ ራስን መቻል የኢትዮጵያ ዋንኛው የስትራቴጂ ምሰሶ መሆኑና ውጥኑ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ አህጉራዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጿል።
ኢትዮጵያ አፍሪካ ራሷን መመገብ እንደምትችል እያሳየች እንደምትገኝ እና ይህም መጪው ትውልድ የምግብ ዋስትናዋ የተረጋገጠ እና የበለጸገች አህጉር እንዲረከብ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር አመልክቷል።
ኢትዮጵያ በጀመረችው በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ ትልቅ ኩራት ይሰማታል ሲል ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አትቷል።