አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በበጀት ዓመቱ ከጣሪያና ግድግዳ ግብር እስካሁን ከሦስት ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።
በተመሳሳይ በተያዘው በጀት ዓመት ከዚህ በፊት ውዝፍ ዕዳ ከነበረባቸው ባለይዞታዎች ሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አሳውቋል።
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለኢዜአ እንዳሉት የጣራና የግድግድ ግብር በየዓመቱ ከሐምሌ እስከ የካቲት 30 ድረስ ያለ ቅጣት ይከፈላል።
በዚህም ከሃምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን መክፈል ከሚጠበቅባቸው 429 ሺህ 829 ባለይዞታዎች መካከል እስካሁን 246 ሺህ 725 ባለይዞታዎች ወይም 62 በመቶዎቹ ከፍለዋል ብለዋል።
ግዴታቸውን ከተወጡ ባለይዞታዎች ከ3 ቢሊየን 60 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የጣሪያና ግድግዳ ግብርን በወቅቱ የመክፈል ልምድ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፤ ግብራቸውን በወቅቱ ያልከፈሉ ባለይዞታዎች የካቲት 30 ከመጠናቀቁ በፊት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ግዴታቸውን በወቅቱ በማይወጡ ግብር ከፋዮች ላይ በየወሩ እየጨመረ የሚሄድ የአምስት በመቶ ቅጣት እንደሚጣል ተናግረዋል።
ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2016 ዓ. ም የጣራና ግድግዳ ግብር ያልከፈሉ ግብር ከፋዮች ውዝፍ ዕዳቸውን እየከፈሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የጣሪያና ግድግዳ ግብር ውዝፍ ዕዳ ከሶስት ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል።