አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፡- መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበለጠ መደገፍ እንደሚገባቸው የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለፀ።
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትን የላቀ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ያለመ አውደ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ወቅት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ የሁሉንም ርብርብ የሚፈልግ ጉዳይ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ሀገሪቱን እየፈተኑ ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት በእያንዳንዱ የልማትና እድገት ውጥን ውስጥ ትኩረት በመስጠት እየሰራበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ ስትራቴጂዎችንና ዕቅዶችን በመቅረፅ እየተገበረች እንደምትገኝ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ከፍ ብላ እንድትታይ ካደረጉ ተግባራት መካከል አንዱ በሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ባለፉት ስድስት አመታት ከ4o ቢሊየን በላይ የዛፍ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል፡፡
መርኃ ግብሩ የሀገሪቱን የደን ሽፋን በፊት ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም ሚኒስትሯ ገልፀዋል።
ከተረጂነት ለመላቀቅ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሌማት ትሩፋትና የበጋ ስንዴ ልማት ስራዎች የኢትዮጵያን አንገት ቀና ያደረጉ ውጤቶች የተመዘገበባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህምኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመመከት በየመድረኩ ከመሳተፍ ባለፈ ተግባር ተኮር እርምጃ በመውሰድ ምሳሌ ለመሆን መብቃቷን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን የእድገቷ ምሰሶ በማድረግ ለስኬት የሚያግዙ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ወደ ስራ ማስገባቷንም አብራርተዋል፡፡
በሀገሪቱ የፓሪስ ስምምነትን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የ2050 የረጅም ዓመት የአነስተኛ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ስትራቴጂ ሰነድ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱንም ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል አቅም በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ረገድ የሲቪል ማህበሰብ ተቋማት አስተዋጽኦ ጉልህ እንደሆነም ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት፡፡
የሲቪል ማህበሰብ ድርጅቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት በርካታ ስራዎች እያከናወኑ መሆኑን በመልካም አንስተዋል፡፡
ተቋማቱ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቋቋም እየተደረገ ያለውን ተግባር ፋይናንስ በማፈላለግ በበቂ ሁኔታ ሊደግፉ ይገባልም ነው ያሉት።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ የሚገኘውን ችግር ለመመከት በሚደረገው ጥረት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ወጥ በሆነ ስርዓት እና ከመንግስት ጋር መደረግ ባለበት ትብብርና ቅንጅት ልክ ሳይመራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት የሚሰሩበት እድል ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ የዛሬው መድረክ የትውውቅና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቁ ፈጣን እርምጃዎች ላይ መግባባት የሚፈጠርበት ነው ብለዋል።