የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሀገር እድገት መሳለጥ ጉልህ ሚና እንዲኖረው የሚያስችል መሰረት እየተቀመጠ ነው</p>

Feb 21, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡- አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሀገር እድገት መሳለጥ ጉልህ ሚና እንዲኖረው የሚያስችል መሰረት እየተጣለ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ተናገሩ።

ዋና ዳይሬክተሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት፤ በተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ሁሉን አቀፍ ርብርብ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው በዚህ ረገድ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል።

ለአብነትም በጸጥታ፣ በጤና ተቋማት፣ በፋይናንስ፣ በግብርናና ሎጂስቲክስን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም ሥራን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅትም 30 የመንግሥት ተቋማት የሚገለገሉበት የመረጃ ቋት መገንባቱን ጠቁመው መረጃዎችን ለችግር ፈቺ ሥራዎች ጥቅም ላይ ለማዋል እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል።

የፍርድ ቤት አገልግሎትን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ኢኒስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

በድምጽ የተቀዱ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ወደ ጹሁፍ መቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂ መተግበር መጀመሩ ሌላው ትልቅ ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ኃይልን ለማብቃት ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2016 ክረምት ወራት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተውጣጡ 211 ተማሪዎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሮቦቲክስ፣ በሶፍትዌር እና ተያያዥ መስኮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በሦስተኛ ድግሪ መርሃ ግብር ለማስተማርም ሥርዓተ ትምህርት መቀረጹን ጠቁመው ኢኒስቲትዩቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙን አንስተዋል።

በዚህም አዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን መጀመሩን ጠቅሰው፤ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲም በቅርቡ ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀምር ገልጸዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር አሰራሮችን ከመዘርጋት ጀምሮ በመስኩ ጊዜው የሚጠይቀውን እውቀት የታጠቀ የሰው ኃይል የማፍራት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.