አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፦የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዲስ የኢትዮጵያ ኢ -ፓስፖርት ይፋ ማድረጊያ መርኃ ግብር እያካሄደ ነው።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከፍተኛ የደህንነት ደረጃ ያለው አዲስ የኢትዮጵያ ኢ-ፓስፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ይፋ ማድረጊያ መርኃ ግብሩ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ይገኛል።
በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ኢ-ፓስፖርት የአንድን ግለሰብ ባዮሜትሪክ መረጃ ጨምሮ የጣት አሻራዎችን፣ የፊት ለይቶ ማወቂያ እና የኤሌክትሮኒክስ ቺፕስ ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ኢ-ፓስፖርት የኢሚግሬሽን ሂደቶችን የሚያቀላጥፍ ነው ተብሏል።
ኢ-ፓስፖርቱ ሀሰተኛ መረጃዎችን እና ማጭበርበርን ለመከላከል የሚያስችል የላቀ የደህንነት ባህሪያትን ያካተተ ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡትን መመዘኛዎች ያሟላና አለም አቀፍ ተቀባይነትን ያረጋገጠ መሆኑ ነው የተገለጸው።
ኢ-ፖስፖርቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በቶፓን ሴኪዩሪቲ ኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበር አማካኝነት በሀገር ውስጥ መመረቱ በመድረኩ ተነግሯል።