የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ትርፋማነት በማሳደግ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ጨምሯል - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ</p>

Feb 21, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አካታች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የግሉን ዘርፍ ትርፋማነት በማሳደግ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ እና የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል(ዶ/ር) የሁለቱን ሀገሮች የኢኮኖሚ ትብብር በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ በመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ሆነ በግሉ ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ አምጥታለች ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መሰል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ የአሰራር ለውጥ በማድረግ የብዝሀ ኢኮኖሚ እድገት ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመሩን ገልጸው፤ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ተሳትፎ በእጅጉ እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡


የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የብዝሀ ኢኮኖሚ ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንግሊዝና ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ትብብር እንዳላቸው አስታውሰው፤ እንግሊዝ በኢትዮጵያ ለተጀመረው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ታደርጋለች ብለዋል፡፡

የእንግሊዝ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡


የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ ኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን በስፋት ለመጀመር የተቋማት ግንባታና የስልጠና ምዕራፎችን አጠናቃ ወደ ሥራ ገብታለች ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ የኢኮኖሚ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ትብብር እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.