ባህርዳር፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመታገዝ ከ510 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ገለጹ።
የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የነባርና አዲስ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ሁኔታ ግምገማና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በባህር ዳር ከተማ ዛሬ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የቢሮ ሀላፊው አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት ክልሉ በስድስት የልማት ቀጠናዎች እንዲለማና በየአካባቢው ያሉ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች ወደ ስራ እንዲገቡ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በተለይ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማበረታታት ሲባል የክልሉ መንግስት በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ከ3 ሺህ 260 ሄክታር በላይ መሬት በኢንዱስትሪ ዞንነት በመከለልና ከ27 በላይ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በማደራጀት አልሚ ባለሃብቶችን ለመሳብ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የመሬት ዝግጅት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን በማሟላትና ማነቆዎችን የመፍታት ስራ መከናወኑንም አስረድተዋል።
በመሆኑም በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ሰፊ መነቃቃት እየተፈጠረ መምጣቱን ገልጸው ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ510 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ ወደ ማምረት ገብተዋል ብለዋል።
በዚህ በጀት ዓመት ብቻ ከ111 በላይ ኢንዱስትሪዎች ምርት እንዲጀምሩ መደረጉን ገልጸው ምርት መጀመር ብቻ ሳይሆን በተለይ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥና ተኪ ምርቶችን በማምረት አበረታች ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።
የወጪ ምርቶችን በማምረትና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር አምራች ኢንዱስትሪው ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ሰፊ መነቃቃት መታየቱን ጠቁመው በኢንዱስትሪዎች መካከል ያለው ጤናማ ፉክክር እየጨመረ መምጣቱ የማምረት አቅማቸውም እያደገ ነው ብለዋል።
አቶ እንድሪስ እንደገለጹት ከ2014 ዓ.ም ወዲህ እስካሁን ባለው የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 59 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው በበኩላቸው በዚህ አመት በማምረቻ ዘርፉ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምርት ተመርቷል ብለዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ እየሄዱበት ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን ገልጸው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት በኩል የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልሉ የዘርፉ ከፍተኛ አሠራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።