ሐረር፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የቀጣይ የዐቢይና ረመዳን ጾሞችን ተከትሎ የምርትና ሸቀጥ አቅርቦት ለመጨመር የቅዳሜና እሁድ ገበያ ከእሁድ እስከ እሁድ እንደሚቀጥል የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ ገለፀ።
በክልሉ መጪዎቹ የፆም ወራት የምርትና ሸቀጥ እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።
በክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ የንግድ ምዝገባ፣ ፍቃድና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሚሊዮን ጽጌ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የዐብይ እና ረመዳን ፆም ወራት በገበያ ላይ የምርትና የሸቀጥ እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።
የቅዳሜና እሁድ ገበያ የተረጋጋ የገበያ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ በዚህም በቀጣይ የፆሙ ወራት ከእሁድ እስከ እሁድ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የሸቀጦች ዋጋን ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በዘይት ምርት ከመሸጫ ዋጋ ተመን ወጭ ጭማሪ ያደረጉ 10 የንግድ ተቋማት እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
በግብርና ምርቶችና ሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ገበያው እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ አካላት ላይ ኤጀንሲው የሚያከናውነውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።