አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2017(ኢዜአ)፦ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለአካታች የፋይናንስ ሥርዓት ግንባታና ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና ባንኮች ገለጹ።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ከወለድ ነፃ ፋይናንስ ኮንፍረንስ እና ሽልማት መርሐግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስኪያጅ ሃጅ ካሚል ሀሩን፥ ለዜጎች አማራጭና አካታች የፋይናንስ ስርዓትን ለመገንባት ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት መጀመሩን አውስተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለአካታች የፋይናንስ ሥርዓት በተሰጠው ትኩረት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች መከፈታቸውንም ተናግረዋል።
ይህም የለውጡ መንግሥት ለአካታች ፋይናንስ ሥርዓት መጎልበት የሰጠውን ትኩረት ያመላክታል ብለዋል።
የኮንፈረንሱ አስተባባሪ አቶ ነብዩ ሁሴን በኮንፈረንሱ ላይ በርካታ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም የሶማሊያ፣ የጅቡቲና የሱዳን የፋይናንስ ተቋማት መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሰፊ እድሎችና ልምዶችን መቀመር የተቻለበት እንዲሁም በዘርፉ የላቀ አፈጻጸምና ክንውን ላስመዘገቡ የፋይናንስ ተቋማት እውቅና የተሰጠበት ነው ብለዋል።
በቀጣይ በመላው ዓለም ያሉ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በማካተት ኮንፈረንሱና የሽልማት መርሐግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን በበኩላቸው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አካታች ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የሲቢኢ ኑር አገልግሎትን ለደንበኞች ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም ዜጎች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ለሀገራቸው የኢኮኖሚ ዕድገት በንቃት እንዲሳተፉ እያድረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሲንቄ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አወል ዝናቡ፥ ባንኩ የሸሪአ ህግን መሰረት በማድረግ ሲንቄ ኢሳን በሚል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ባንኩ አገልግሎቱን ለመደበኛ የባንክ ደንበኞችና ለአነስተኛ መካከለኛ የቢዝነስ ተቋማት ተደራሽ በማድረግ ለአካታች ሀገራዊ ልማት አስተዋፅኦ እያደረገ ነው ብለዋል።