የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

<p>ኢትዮጵያና ቻይና የኢንቨስትመንት ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ</p>

Feb 25, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤የካቲት 17(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ቻይና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።


የኢትዮ- ቻይና የ2025 የኢኮኖሚ እና ንግድ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት የተመቸ ነባራዊ ሁኔታ አላት።


ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ልማትን በማፋጠን ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።


በለውጡ አካታችና ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር መፈጠሩን የገለፁት ኮሚሽነሩ፥ በዚህም የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስት እያደረጉ ነው ብለዋል።


ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በአይ ሲ ቲ፣ በቱሪዝም እና ግብርና እና በማዕድን ዘርፎች ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሏት ገልጸዋል።


በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር በፈጣን እድገት ላይ መሆኑን ገልጸው፥ የቻይና ባለሀብቶች እድሉን አጠናክረው ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።


በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።


በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ኤዥያና ፓስፊክ ሀገሮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ንጉስ ከበደ፥ ኢትዮጵያ እና ቻይና በተለያዩ ማዕቀፎች ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ እና ቻይና ንግድና ኢንቨስትመንት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ ትብብር መሆኑንም ጠቁመዋል።


ሁለቱ ሀገራት ከንግድና ኢንቨስትመንት ባለፈ በታዳሽ ኃይል፣ በህብተሰብ ጤና፣በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ እና መሰል ዘርፎች ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ፥ ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ እና በባህላዊ ሀብቶች የታደለች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።


ኢትዮጵያ እና ቻይና የላቀ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ተጨማሪ የትብብር አቅምን ያሳድጋል ብለዋል።


የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስታወቂያ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ቼን ጂያንአን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካና በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኗን ጠቅሰዋል።



በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብር ትልቅ እድገት እያሳየ መምጣቱንም ገልጸዋል።


በአፍሪካ ፈጣን እድገት የምታስመዘግብ፣ለሮድ ኤንድ ቤልት ኢኒሼቲቭ ውጤታማነት የጎላ ሚና ያላትና የቻይና ወሳኝ አጋር መሆኗንም አንስተዋል።


ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማጠናከር እንደምትሻ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.