አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የሴት ነጋዴዎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ሲሉ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
መንግስት ለማህበሩ ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የቦርድ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሴቶች የንግድ እንቅስቃሴ እና ተሳትፎ ላይ ያተኮረ መሆኑን ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ማህበሩ ህጋዊ መሰረት በመያዝ የሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር ተወካዮችን ባካተተ መልኩ በአዲስ መልክ መደራጀቱ መልካም የሚባል እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች በሀገር አቀፍ፣ አህጉርና አለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ማሳደግ እና ጠንካራ ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ማህበሩ ሴት ነጋዴዎች እየተከፈቱ ባሉ አዳዲስ የንግድና ገበያ ዕድሎች ውስጥ በመሳተፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
በተለይም በአነስተኛ የንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው እየተጉ ያሉ ሴቶችን በማብቃት የሴቶችን የተሳትፎ መሰረት ማስፋት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የሴቶች ተሳትፎ ለአካታች ኢኮኖሚና ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ ረገድም ሚኒስቴሩ ለማህበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።