ሐዋሳ፤የካቲት 19/2017 (ኢዜአ):-በክልሉ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የግብርና ልማትን ጨምሮ በከተማ ልማትና ሌሎችም ዘርፎች ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ በዛሬው እለት ያካሄደ ሲሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የስድስት ወራት አጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በክልሉ በመስኖ ልማት፣በሌማት ትሩፋት፣የከተማ ልማት እንዲሁም በእንስሳት ልማት ዘርፍና አጠቃላይ በግብርና ልማት የተከናወኑ ተግባራት ትልቅ ስኬት የተመዘገበባቸው መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በ8 ኢኒሼቲቮችና በ68 ፓኬጆች የያዘ ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ ወደ ስራ እንደተገባም ገልጸዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለመሻት የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ጠቅሰው፥ ገበያን በማረጋጋት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለልም ብዙ ርቀት መኬዱን ተናግረዋል።
የእንስሳት እርባታና ሌሎች የግብርና ስራዎች ላይ በማተኮር የተከናወነው ስራም ውጤታማ መሆኑን አንስተዋል።
በገቢ አሰባሰብ ረገድም በስድስት ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 97 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በከተማና በገጠር መንገድ ተደራሽነት፣በኮሪደር ልማትና በመጠጥ ውሃ አቅርቦትም የተያዘው እቅድ የተሳካበት ነው ብለዋል።
የምክር ቤቱ ስብሰባ በዛሬ ውሎው የርዕሰ መስተዳድሩን ሪፖርት ካደመጠ በኋላ አፈጻጸሙን የገመገመ ሲሆን በነገው እለትም የተለያዩ አዋጆችን እንዲሁም ሹመቶችን በማፅደቅ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።