አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፡- የዓድዋ ድል እና የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በየዘመናቸው በአብሮነት ያሳኳቸው ዘመን ተሻጋሪ ድሎች ናቸው ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለፁ።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ተባብረው ለሀገራቸው ዘመን ተሻጋሪና ለሌሎችም አርአያ የሚሆኑ ተግባራትን በመፈጸም እንደቀጠሉ ናቸው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) የዓድዋ ድልን እና የዘመኑ የአርበኝነት ተምሳሌት የሆነው የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ተምሳሌት፤ የአይቻልም አስተሳሰብን በማሸነፍ በተግባር ያረጋገጡበት ለመጪው ትውልድ ትልቅ ታሪክ ነው ብለዋል።
መላው ኢትዮጵያውያን ከህፃን እስከ አዋቂ ከሀገር እስከ ውጭ በጋራ ርብርብ ያገባደዱት የዘመናችን አሻራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዓድዋ ድልም ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል በማድረግ ለመላው የአለም ጥቁር ህዝቦች ጭምር ኩራት የሆነ ዘመን ተሻጋሪ ድል እንደሆነ አንስተዋል።
የህዳሴ ግድብንና የዓድዋ ድልን በርካታ የሚያመሳስላቸው ነገሮች እንዳሉ ገልጸው፤ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን በወኔ፣ በጀግንነት እና በህብረ ብሔራዊ አንድነት የተጎናጸፉት ድል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው የፋይናንስ አቅም አንድነታቸውን በማጠናከር ዘመን ተሻጋሪ ድል አድራጊነትን ያሳዩበት ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል የውጫሌ ስምምነትንና ቀኝ ገዥዎች በጥቁር ህዝቦች ላይ የነበራቸውን ያልተገባ አስተሳሰብ ያሸነፈ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ህዳሴ ግድብም በአባይ ወንዝ ላይ ያዘጋጀናቸውን ሰነዶች በትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እና የህዳሴ ግድብን በመገንባት ዳግም ድል የተጎናፀፍንበት ነው ሲሉም ገልፀዋል።
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሃሳብ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል፡፡