አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- ሁለተኛው ያልተማከለ የአደጋ አስተዳደር ስጋት ቅነሳ ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም(ዶ/ር) ፕሮጀክቱ ይፋ በሆነበት ወቅት እንደገለጹት፤ ለሁለተኛው ያልተማከለ የአደጋ አስተዳደር ቅነሳ ፕሮጀክት ከአውሮፓ ሕብረት 20 ሚሊዮን ዩሮ ተግባራዊ ይደረጋል።
ለዜጎች የሚሰጡ ሰብዓዊ ድጋፎች ዜጎችን በዘላቂነት ማቋቋም እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ በዘጠኝ ክልሎች ለአራት ዓመታት እንደሚተገበር ጠቁመው፤ ከፕሮጀክቱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የአውሮፓ ሕብረት ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ፕሮጀክት ስጋትን በመከላከል ተግባር ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ከቤተሰብ ጀምሮ አካባቢና የአካባቢ መዋቅርን አቅም በመፍጠር ለአደጋ ስጋት አይበገሬነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በአምስት ክልሎች የራሱ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው፤ መንግስት አደጋዎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅምን በማሳደግ ረገድ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው እለት በይፋ የተጀመረው የአውሮፓ ሕብረት ፕሮጀክት ለአደጋ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጋር የተጣጣመ ለማድረግ የሚያግዝ ነው።
የአውሮፓ ሕብረትና ሌሎች የልማት አጋር አካላትም አደጋን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕብረቱ ለሁለተኛው ዙር ያልተማከለ የአደጋ አስተዳደር ስጋት ቅነሳ ፕሮጀክት የሰጠው ድጋፍም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን ቡድን የትብብር ኃላፊ ሮቤርቶ ሰኪሎር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ሕብረት ያልተማከለ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ላይ ያሏዋቸው ፖሊሲዎች ተጣጥመው የሚሔዱ ናቸው።
በሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት ቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ ባለፉት አራት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የመጀመሪያው ምዕራፍ ፕሮጀክት ስኬታማ መሆኑን ገልፀዋል።