የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የሀገራችንን የንግድ ስርዓት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው - የንግዱ ማህበረሰብ አባላት</p>

Mar 3, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2017(ኢዜአ)፡- የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የአሀገራችንን የንግድ ስርዓት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን ትናንት መርቀው ከፍተዋል።

የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት በዛሬው እለት የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

ኢዜአ ካነጋገራቸው የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ ደስታ ወለጋ፤ ማዕከል የሀገራችንን የንግድ ስርዓት ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር የንግድ ማህበረሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት ለመጪው ትውልድም የሚተርፉ መሆናቸውን መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች ለዓለም በማስተዋወቅ የንግድ ስርዓቷን የምታሳድግበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የጉብኝቱ ተሳታፊ አቶ ሙሉጌታ መስፍን ናቸው።

በተለይም ከዚህ በፊት እንደ ከተማ የነበሩ የአገልግሎት ጉድለቶችን በመሙላት ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ በብዛት እንዲመጡና የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ የሚያድርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ ኢንተርናስናል ኮንቬንሽን ማዕከል የሀገሪቱን እድገት የሚያሳልጥ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጉብኝቱ ተሳታፊ ወይዘሪት ሸዋ ጎፋ ናቸው፡፡

በአጭር ጊዜ ይህን ያህል ግዙፍ ማዕከል ተገንብቶ ማየታቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቱ አባል አቶ ሚካኤል ተክሌ በበኩላቸው፤ የማዕከሉ ግንባታ ኢትዮጵያን የቱሪዝም ኮንፍረንስ ማዕከል ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የንግዱ ማህበረሰብን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር የዘመነ የንግድ ስርዓት እንደዘረጋ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ 40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው 2 ትላልቅ አዳራሾች፣ 8 አነስተኛ እና መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾች በጠቅላላ እስከ 10 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግዱ አዳራሾችን የያዘ ነው።

ማዕከሉ ዘመናዊ ሆቴልን፣ ሪስቶራንቶችን፣ ሾው ሩሞችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎችን በአንድ ያካተተ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.