መቱ፤ የካቲት 24/2017 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል የግብርና ልማት ሥራን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በኢሉባቦር ዞን አሌና ቡሬ ወረዳዎች በማር ምርት እና በስንዴ ልማት እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅት ኃላፊው እንደገለጹት በክልሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተከናወኑ ባሉ የግብርና ፕሮግራሞች አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል።
ፕሮግራሞቹን ይበልጥ በማስፋፋት አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርቶቹን ወደውጭ ልኮ ገቢውን እንዲያሳድግ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"በግብርና ልማት ትኩረት ከተሰጣቸው አንዱ የማር ምርትና ምርታማነትን መጨመር ነው" ያሉት አቶ ጌቱ በመስኩ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በተያዘው ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅስዋል።
በዞኑ ቡሬ ወረዳ ነቦ ምሪጋ ቀበሌ በኩታ ገጠም እየለማ ያለው የስንዴ ልማትም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አቶ ጌቱ ተናግረዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በኢሉባቦር ዞን 240 ዘመናዊ ቀፎዎች ብቻ እንደነበሩ ያስታወሱት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።
"ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለግብርና ዘርፍ በሰጠው ትኩረትና በተሰራው ሥራ በአሁኑ ወቅት 340 ሺህ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ተችሏል" ብለዋል።
በተያዘው ዓመት 16 ሺህ ቶን ማር ለማምረትና ምርቱንም ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደ አንድ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ በዞኑ በተያዘው የበጋ ወቅት 96 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል እየለማ ይገኛል።
በአሌ ወረዳ በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩት አቶ ታከለ ማሞ 140 ዘመናዊ፣ ባሕላዊና የሽግግር ቀፎዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል።
በተሰማሩበት የንብ ማነብ ሥራ ምርታማነታቸውንና ገቢያቸውን በማሳደግ ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሸጋገር አቅደው እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በስንዴ ልማት የተሰማሩት የነቦ ምሪጋ ቀበሌ ነዋሪዎችም በበኩላቸው አሁን እየለማ ከሚገኘው ስንዴ ጥሩ ምርት ለማግኘት ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።