የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

<p>በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ከማዕድን ልማት 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል</p>

Mar 5, 2025

IDOPRESS

ዲላ፤ የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ከማዕድን ልማት 100 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ በማዕድን ልማት የተሰማሩ ድርጅቶች ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተጣጣመ ሥራ እንዲሰሩ የቅርብ ክትትል እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።

የቢሮው ምክትልና የማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሄሌን ዮሐንስ እንደገለጹት በክልሉ ያሉ የከበሩ፣ የጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድናትን ለማልማት እየተሰራ ነው።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራት ከ147 ሺህ 200 ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል እና ዶሎማይት በማምረት ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መቅረቡን ተናግረዋል።

በዚህም ከውጭ የሚመጣን ምርት ለመተካት መቻሉን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ በድንጋይ ከሰል ምርት ወደ ሥራ የገቡ 14 ድርጅቶች በሀገሪቱ ለሚገኙ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው።

በኤክስፖርት እንቅስቃሴም ከ29 ቶን በላይ የጌጣጌጥ ማዕድን ለገበያ መቅረቡን ጠቅሰዋል።

በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ከማዕድን ልማት 100 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የተናገሩት ወይዘሮ ሄለን፣ በዘርፉም ከ12 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

ወደክልሉ መጥተው በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ክልሉ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 2 የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎችን ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው ያሉት ሃላፊዋ፣ ይህም ክልሉ ከዘርፉ ያለውን ተጠቃሚነት ያሳድገዋል ብለዋል።

በክልሉ ያሉትን ሀብቶች ለመጠቀም የህግ ማዕቀፎችን ከመተግበር ባለፈ የተቀላጠፈ አገልግሎት መዘርጋቱን ጠቅሰዋል።


በክልሉ የማዕድን አልሚዎች ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚጣጣም ልማት እንደሚያከናውኑ ተረጋግጦ ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ደን አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ ናቸው።

በተለይ የማህበረሰቡን ደህንነትና ጤንነት ከመጠበቅ ባለፈ ስነ ምህዳርንና ነባር ዛፎችን እንዲንከባከቡ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል

በጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ የቱሳ የማዕድን ቁፋሮ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ጎንጮ በበኩላቸው በወረዳው በድንጋይ ከሰል ቁፋሮ ተሰማርተው ምርታቸውን ለኢንዱስትሪዎች እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀን ከ10 ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ለገበያ በማቀረብ እራሳቸውንና አካባቢያቸውን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አንስተዋል።


በዚህም ከ300 ለሚበልጡ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ በምርት ወቅት ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ቅድሚያ እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

በአካባቢው የማዕድን ቁፋሮ ልማት መጀመሩ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የተናገረው ደግሞ የቦረዳ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ዳዊት ማሞ ነው።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ እሱን ጨምሮ 67 ወጣቶች በከባድ መኪና አቅርቦት ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሷል።

ይህም ከአካባቢው ሳይርቅ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.